Thursday, August 27, 2020

አክስዮን በመያዣነት ስለሚሰጥበት ሁኔታ-ሰ/መ/ቁ. 39191

 

የሰ/መ/ቁ. 39191

ሐምሌ 2 ቀን 2001 ዓ.ም

 ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ

       መንበረፀሐይ ታደሰ

       ዓብዱልቃድር መሐመድ

       ፀጋዬ አስማማው

       ዓሊ መሐመድ

አመልካች፡- አቶ አበባው ደስታ ጠበቃ አቶ አምሣለ ፀሐይ ቀረቡ

ተጠሪ፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነገረፈጅ አቶ ደረጀ ባዩ ቀረቡ

      መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

ፍ ር ድ

      ጉዳዩ የቀረበው አመልካች በከፍተኛው ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 62615 ግንቦት 13 ቀን 2000 ዓ.ም የሰጠው ትእዛዝና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 38765 ሰኔ 25 ቀን 2000 ዓ.ም የሰጠው ትእዛዝ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት ስላመለከተ ነው፡፡

      የክርክሩ መነሻ በዚህ ክርክር ተካፋይ ያልሆነውና አመልካችን ከስሶ የፍርድ ባለመብት የሆነው አቶ መሰረት መላኩ ያቀረበው የአፈፃፀም ክስ ነው፡፡ የፍርድ ባመብቱና አመልካች ከፍርድ ቤት ውጭ አፈፃፀሙን ለመጨረስ ተስማምተዋል፡፡ የፍርድ ባለመብቱና አመልካች ባደረጉት ስምምነት አመልካች በአቢሲኒያ ባንክ (አ.ማ) እና በናይል ኢንሹራንስ(አ.ማ) ያለው የአክስዮን ድርሻ ለፍርድ ማስፈጸሚያ ሆነው ለአፈፃፀም ከሳሽ እንዲተላለፍ ተስማምተዋል፡፡ ይህንንም ስምምነታቸውን ፍርድ ቤት አቅርበው ፍርድ ቤቱ በስምምነታቸው መሰረት እንዲፈፀም ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡     ተጠሪ አመልካችና የስር አፈፃፀም ከሳሽ ያደረጉት ስምምነትና የስር ፍርድ ቤት የሰጠው የአፈፃፀም ትእዛዝ አመልካችና ባለቤታቸው ወ/ሮ ትእግስት ወንድይፍራው ግንቦት 16 ቀን 1993 ዓ.ም በተፈረመ የመያዛ ውል፣

   ጭስ አባይ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጥር 25 ቀን 1992 ዓ.ም ለወሰደው ብር 50,000,000(ሃምሣ ሚሊዮን ብር) ብድር ይኸው የንግድ ድርጅት የካቲት 16 ቀን 1993 ዓ.ም ለወሰደው ብር  50,000,000(ሃምሣ ሚሊዮን ብር) ብድርና የካቲት 16 ቀን 1993 ዓ.ም ለወሰደው ብር 10,000,000(አስር ሚሊዮን) ኦቨር ድራፍት ብድር መያዣ እንዲሆን ዋጋቸው ብር 1,627,000(አንድ ሚሊዮን ስድስት መቶ ሃያ ሰባት ሺ ብር) የሆነ በናይል ኢንሹራንስ (አ.ማ) ያሏቸውን 1627 አክሲዮኖችና ጠቅላላ ዋጋቸው 750,000(ሰባት መቶ ሐምሳ ሺ ብር) የሆነ በአቢሲኒያ ባንክ(አ.ማ) ያሏቸውን 750 አክሲዮኖች በመያዣነት አስይዘዋል፡፡ መያዣውም በናይል ኢንሹራንስ (አ.ማ) እና አቢሲኒያ ባንክ (አ.ማ) የአክሲዮን መዝገብ ተመዝግቧል፡፡ ስለሆነም የአፈፃፀም ከሳሽ ከአመልካች ጋር ያደረጉት የአፈፃፀም ስምምነትና ፍርድ ቤቱ የሰጠው ትእዛዝ በአክሲዮን ድርሻዎቹ ላይ ያለንን የመያዣና የቀዳሚነት መብት የማያሣጣ በመሆኑ እንዲሰረዝልን በማለት የሰነድ ማስረጃዎቹን በማያያዝ፣በክርክሩ ጣልቃ ገብቷል፡፡

      አመልካች በናይል ኢንሹራንስ (አ.ማ) እና አቢሲኒያ ባንክ  (አ.ማ) ያሉኝን የአክሲዮን ድርሻዎች በጉዳዩ ገዥነት ያላቸው የሕግ ድንጋጌዎች የሚጠይቁትን ፎርማሊቲ በማሟላት የፈፀምኩት የመያዛ ውል የለም፡፡ ጭስ አባይ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የኦቨር ድራፍት ውል ስዋዋል የአክሲዮን ድርሻዎችን በመያዣ ሰንጠረዝ አላስመዘገብኩም፡፡ ሰነዶቹ በፖሊስ ተወስደው ስለነበርና በመያዣ ሰንጠረዥ ተገልፀዋል ቢባል እንኳን የመያዣ ፎርም ስለማያሟላ ውጤት የለውም በማለት ተከራክረዋል፡፡ የስር ፍርድ ቤት በአመልካችና በተጠሪ በኩል የቀረበውን ክርክርና ማስረጃ ከመረመረ በኋላ  ጭስ አባይ ኃላፊነቱን የተወሰነ የግል ማህበር የካቲት 16 ቀን 1993 ዓ.ም የብር 10,000,000 (አስር ሚሊዮን ብር) የኦቨር ድራፍት ብድር ለመበደር በተዋዋለው ውል አመልካች በናይል ኢንሹራንስ (አ.ማ) ያሉትንና ዋጋቸው 1,627,000 (አንድ ሚሊዮን ስድስት መቶ ሃያ ሰባት ሺ ብር) የሆነ 1627 አክሲዮኖችና በአቢሲኒያ ባንክ አ.ማ ያለንና ዋጋቸው 750,000(ሰባት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር) የሆነ 750 አክሲዩኖች በመያዣ ሰንጠረዡ ላይ አስመዝግቦ ያስያዘ በመሆኑና ውሉም የፍታብሔር ሕግ ቁጥር 1725 እና የፍታብሔር ሕግ ቁጥር 2828 ፎርም ያሟላ ስለሆነ በእነዚህ አክስዮኖች ላይ አመልካች የመያዝና ቀዳሚነት መብት አለው በማለት ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡ አመልካች በዚህ ትእዛዝ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ችሎት አቅርበው ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ የስር ፍርድ ቤት ውሣኔ የሚነቀፍበት ምክንያት የለም በማለት ይግባኙን ሰርዞታል፡፡ አመልካች የስር ፍርድ ቤት የሕጉን ፎርም የሚያሟላ የመያዣያ ውል ሣይቀርብለትና ገዥነት ያላቸውን የሕግ ድንጋጌዎች በመተላለፍ የመያዣ ውል አለ በማለት የሰጠው ትእዛዝ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት አመልክቷል፡፡ ተጠሪ በበኩሉ አመልካች አክሲዮኖቹን በመያዣነት በነፃ ፈቃዱ ያስያዘ መሆኑን የሚያሣይ ማስረጃ አቅርበናል፡፡ አክሲዮኖቹ በመያዣነት የተያዙ ስለመሆኑ በአክሲዮን መዝገብ ተመዝግቧል፡፡ አመልካች አክስዮኖቹ የተጠሪ መያዣ እንደሆኑ በማመን ተጠሪ በባለ አክሲዮኖች ስብሰባ ለመካፈል እንዲፈቅድለት የጠየቀበትን ደብዳቤ በማስረጃነት አቅርበናል፡፡ የስር ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚው ችሎት የፈጸሙት የሕግ ስህተት የለም በማለት መልስ ሰጥቷል፡፡ ይግባኝ ባይ የመልስ መልስ ሰጥቷል፡፡

      በስርና በሰበር የቀረበው ክርክርና የስር ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት የሰጡት ትእዛዝ ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም ግዙፍ ያልሆኑ ሐብቶች (ኢንታጀብል)በመያዣነት ሲያዙ ተፈፃሚ ስለሚሆነው የሕግ ክፍልና የህግ ድንጌዎች ይኸ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 39256 የሰጠውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም መሰረት በማድረግ የአመልካችንና የተጠሪን ክርክር እና የስር ፍርድ ቤት ትእዛዝ መርምረናል፡፡

      የባለአክሲዮኑ ስም የተፃፈባቸውን የአክሲዮን ድርሻዎች በመያዣነት ለመያዝ በፍታብሔር ሕግ ቁጥር 2865 ንኡስ አንቀጽ 1 እና በፍታብሔር ሕግ ቁጥር 341 ንኡስ አንቀጽ 2 የተደነገገው ፎርማሊቲ መሟላት እንዳለበት ከላይ ቁጥሩ በተገለፀው መዝገብ ሰፊ ትንታኔ ተሰጥቶበታል፡፡ ከዚህ አንፃር ስንመዝነው አመልካች በናልይ ኢንሹራንስ(አ.ማ) ያሉትን 1627 አክሲዮኖች እና በአቢሲኒያ ባንክ (አ.ማ) ያሉትን 750 አክሲዮኖች በተጠሪ በመያዣነት ያያዛቸው መሆኑን እና መያዣውም በናይል ኢንሹራን (አ.ማ) እና አቢሲኒያ ባንክ(አ.ማ) አክሲዮን መዝገብ የተመዘገበ መሆኑን የሚያረጋግጥ የጽሑፍ ማስረጃ አቅርቧል፡፡ ይኸም ተጠሪ በሁለቱ ካንፓኒዎች ያሉትን የአክሲዮን የድርሻዎች ተጠሪ የፍታብሔር ሕግ ቁጥር 2865 ንኡስ አንቀጽ 1 እና በንግድ ሕግ ቁጥር 341 ንኡስ አንቀጽ 2 የተደነገገውን ፎርማሊቲ በማሟላት አክሲዮኖቹን በመያዣነት የያዣቸው መሆኑን የሚያስረዳ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

      ተጠሪ ከላይ ቁጥራቸውና ዋጋቸው የተገለጸውን የአመልካች አክሲዮኖች በመያዣነት የያዘው በአመልካች ሙሉ ስምምነትና ፈቃድ መሰረት መሆኑን የሚያስረዱ የጽሑፍ ማስረጃዎችን አቅርቧል፡፡ አመልካች ጭስ አባይ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ከተጠሪ ብር 10,000,000(አስር ሚሊዮን ብር) በኦቨር ድራፍት ብድር ሲወስድና የብድር ውሉን ስዋዋል በናይል ኢንሹራንስ(አ.ማ) ያሉትን ዋጋቸው 1,627,000 (አንድ ሚሊዮን ስድስት መቶ ሃያ ሰባት ሺ ብር) እና በአቢሲኒያ ባንክ(አ.ማ) ያሉትን ዋጋቸው 750,000(ሰባት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር) የሆኑ አክሲዮኖች በውሉ የመያዣ ሰንጠረዥ በማስመዝገብ ውሉን የፈረመ መሆኑን የሚያሣይ ማስረጃ ተጠሪ አቅርቧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አመልካች ተጠሪ በባለአክሲዮኖች ስብሰባ ለመካፈል እንዲችል እንዲፈቀድለት የፃፈው ደብዳቤና ሌሎች የሰነድ ማስረጃዎች ተጠሪ የአመልካችን አክሲዮኖቹ በመያዣነት የያዘውና የፍታብሔር ሕግ ቁጥር 2865 ንኡስ አንቀጽ 2 መሰረት በአመልካች ፈቃድና ስምምነት መሰረት መሆኑን የሚያስረዱ በቂ ማስረጃዎች ናቸው፡፡

      ጉዳዩን በመጀመሪያና በይግባኝ ያዩት ፍርድ ቤቶች ተጠሪ በአመልካች አክሲዮኖች ላይ ህጋዊ የመያዣ ውልና የቀዳሚነት መብት አለው በማለት ውሣኔ የሰጡት የአክሲዮን ድርሻን እንደማንኛውም ግዙፍነት ያለው ተንቀሣቃሽ ንብረት በመቁጠር ግዙፍነት ያላቸውን ንብረቶች ስለመያዝ የተደነገጉትን የፍታብሔር ድንግጌዎች በተለይም የፍታብሔር ሕግ ቁጥር 2828 እና ሌሎች ጠቅላላ የውል ሕግ ድንጋጌዎች መሰረት በማድረግ ነው፡፡ አመልካች በአቢሲኒያ ባንክ(አ.ማ) እና በናይል ኢንሹራንስ(አ.ማ) በባለቤትነት የያዛቸው አክሲዮኖች የራሳቸው ልዩ ባህሪና ውጤት ያላቸው ግዙፍ ያልሆኑ ሐብቶች (ኢንታንጀብልስ) ናቸው፡፡ እነዚህ ግዙፍ ያልሆኑ ሐብቶች በማዣነት ስለሚያዙበት ሁኔትና መያዣው ስለሚያስከትለው ውጤት ገዥነት ያላቸው የሕግ ድንጋጌዎች ከፍታብሔር ሕግ ቁጥር 2863 እስከ ፍታብሔር ሕግ ቁጥር 6874 ተደንግገው ይገኛሉ፡፡ የስር ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት ለውሣኔቸው መሰረት አድርገው የጠቀሱት ግዙፍነት ያላቸው ተንቀሣቃሽ ንብረቶች በመያዣነት ስለሚያዙበት ሁኔታ የሚደነግገውን የሕግ ክፍል ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

      ስለሆነውም የስር ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት ተጠሪ በአመልካች የአክሲዮን ድርሻዎች ላይ የመያዣያ መብት አለው በማለት የደረሱበት መደምደሚያ ትክክል ስለሆነ ፍርድ ቤቶቹ ለውሣኔቸው መሰረት አድርገው የጠቀሷቸው የሕግ ድንጋጌዎች ከጉዳዩ ጋር አግባብነት የሌላቸው መሆኑን በመገንዘብና ሕጉን በመተርጐም እረገድ የፈፀሙትን ስህተት ከላይ በተገለፀው መንገድ በማሻሻል በውጤት ደረጃ የስር ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት የደረሱበትን መደምደሚያ አጽንተነዋል፡፡

ው ሳ ኔ

1.  የከፍተኛው ፍርድ ቤትና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጡትን ውሣኔ ምክንያቱ ብቻ ተሻሽሎ ጸንቷል፡፡

2.  አመልካችና ተጠሪ ወጭና ኪሣራ ለያራሳቸው ይቻሉ

ይህ ፍርድ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በሙሉ ድምጽ ተሰጠ፡፡

                                      የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት

ቤ/ኃ       

No comments:

Post a Comment

Cancellation of Contracts

   Cancellation of Contracts Cancellation is another remedy for non-performance. Cancellation brings an already existing contract to an end....