Wednesday, August 26, 2020

የባንክ ብድር- የአንድነትና ነጠላ ዋስትና -ሰ.መ.ቁ 44088

 

      የሰ.መ.ቁ 44088

ሐምሌ 27 ቀን 2002 ዓ.ም

 

 

ዳኞች፣ ሐጐስ ወልዱ

                                  ሂሩት መለሰ

                                  ብርሃኑ አመነው 

    አልማው ወሌ

    ዓሊ መሐመድ 

 

 

አመልካች፣  አጋር ማይክሮ ፋይናንስ አ/ማ እርገጤ መድበው ቀረበ

ተጠሪዎች፣  1. ፍቅሬ ሽብሩ

2.    አንተነህ ታደለ

3.    አስፋው ገ/ስላሴ

4.    ፍቃዱ ነጋ

5.    እሸቱ ገ/ስላሴ  

 

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን  ፍርድ ሰጥተናል፡፡

 

   

 

 ለሰበር አቤቱታው መነሻ የሆነው ጉዳይ በብድር የተሰጠን ገንዘብ ይመለስ በሚል የቀረበውን ክስ የሚመለከት ነው ክሱን በመጀመሪያ ደረጃ ያስተናገደው የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ሲሆን ከሣሽ የነበረው አመልካች ነው አመልካች አምስቱንም ተጠሪዎች በአንድነት አጣምሮ የከሰሰው 1ኛ ተጠሪ ብር 5000 ተበድሮአል የተበደረውን ገንዘብ በሙሉ አልመለስም ከ2 እስከ 4 ያሉት ተጠሪዎች የአንድነት እና የነጠላ ዋሶች ናቸው 5ኛ ተጠሪም የጠለፋ ዋስ ነው በማለት ነው ከ3ኛ እና 5ኛ ተጠሪዎች በስተቀር ሌሎቹ ቀርበው በቀረበው ክስ ላይ መልስ ሰጥተዋል ሁሉም ገንዘቡ በብደር መውሰዱንና ዋሶች መሆናቸውን አልካዱም በሌላ በኩል ግን 1ኛ ተጠሪ በብድር የወሰደው ገንዘብ ለ3ኛ ተጠሪ አሳልፎ ሰጥቻለሁ ይህም በወቅቱ የከሣሽ ሥራ አስኪያጅ የነበረው ግለሰብ አውቆት ተቀብሎታል በማለት ሲከራከር ሌሎቹም በአንድ በኩል የ1ኛ ተጠሪን የመከራከሪያ ነጥብ በመጥቀስ በሌላ በኩል ደግሞ 1ኛ ተጠሪ በቂ ሥራ ስላለው መጠየቅ ያለበት እሱ ብቻ ነው ነው በማለት ተከራክረዋል ክርክሩ በዚህ መልክ ከተጠናቀቀ በኃላ፣ ፍ/ቤቱ ገንዘቡን መክፈል ያለበት 3ኛ ተጠሪ ነው እሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል የሚከፈለው የገንዘብ መጠንም ብር 6424.76 /ስድስት ሺህ አራት መቶ ሃያ አራት ብር ከሰባ ስድስት ሣንቲም/ እንደሆነ ገልፆል፡፡ አመልካች በውሣኔው ባለመስማማት ለፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ አቅርቦ የነበረ ሲሆን ፍ/ቤቱም ክርክሩን ከሰማ በኃላ በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ የተሰጠውን ውሣኔ አፅንቶአል የሰበር አቤቱታው የቀረበው በዚህ ላይ ነው፡፡

እኛም አመልካች የካቲት 27 ቀን 2001 ዓ.ም በጻፈው ማመልከቻ ያቀረበውን አቤቱታ መሠረት በማድረግ ክርክሩን ሰምተናል በተደረገላቸው ጥሪ መሠረት የቀረቡት 1ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች ብቻ ናቸው ሌሎቹ በጥሪው መሠረት ባለመቅረባቸው ክርክሩ የተሰማው እነሱ በሌሉበት ነው አቤቱታው በሰበር ችሎት እንዲታይ የተወሰነው በሥር ፍ/ቤቶች የተሰጠው ውሣኔ በፍ/ብ/ሕግ ቁ 1763 እና 1803/2/ እና /3/ የተመለከቱትን ድንጋጌዎች ያገናዘበ መሆን አለመሆኑን ለመመርመር ነው በመሆኑም ይህንን ነጥብ ግራቀኙ ወገኖች ከሰሙት ክርክር አቤቱታ ከቀረበበት ውሣኔ እና ከሕጉ ጋር አገናዝበን መርምረናል፡፡

ለክርክሩ መነሻ የሆነው ገንዘብ ከአመልካች በውል የተበደረው 1ኛ ተጠሪ ነው ከ2 እስከ 5 የተመለከቱት ተጠሪዎች ለብድሩ መመለስ የዋስትና ግዴታ የገቡ ስለመሆናቸውም አልተካደም በብደር ውሉ መሠረት ገንዘቡ እንዳልተመለሰም እንደዚሁ የታመነ ጉዳይ ነው አከራካሪ ሆኖ የቀረበው ለብድሩ ገንዘብ የመጀመሪያው ተጠያቂ ማን መሆን ይገባዋል? የሚለው ነው አመልካች አጥብቆ የተከራከረው በብድር ውሉ እንደተመለከተው ተበዳሪው 1ኛ ተጠሪ በመሆኑ እና ሌሎች ተጠሪዎችም የአንድነት እና የነጠላ ዋስትና ግዴታ ስለገቡ የብድሩ አመላለስም በዚህ መሠረት ነው መወሰን ያለበት በማለት ነው፡፡ ተጠሪዎች ደግሞ የብድር ውሉ በአመልካች ክርክር በተገለጸው አይነት የተደረገ ቢሆንም ተበዳሪው ገንዘቡን ለ3ኛ ተጠሪ የሰጠ በመሆኑ መክፈል/መመለስ ያለበት ገንዘቡን የወሰደው ሰው ነው በማለት ተከራክሮዋል የሥር ፍ/ቤቶችም ይህን የተጠሪዎችን ክርክር በመቀበል ነው የወሰኑት፡፡

በበኩላችን እንደምናየው አመልካች በተበዳሪነት የሚያውቀው 1ኛ ተጠሪን ነው 1ኛ ተጠሪ ብድሩን የወሰደው ሌሎቹን ተጠሪዎች ዋስ በመጥራት ነው በዚህ መልክ የተደረገው ውል ማሻሻል ወይም ቀሪ ማድረግ የሚቻለውም በተመሳሳይ ሁኔታ ማለትም አበዳሪው አክሲዩን ማህበር /አመልካች/ ስምምነቱ በግልጽ በሰጠበት ሁኔታ ብቻ ነው በያዝነው ጉዳይ እንደምናየው አመልካች እና 1ኛ ተጠሪ በመስማማት ውሉን አላሻሻሉም ከፍ ሲል እንደተመለከትነው አመልካች ብድሩን የሰጠው በአመላለሱ ችግር እንዳይፈጠርበት አስቀድሞ ጥንቃቄ በማድረግ ሌሎቹን ተጠሪዎች የዋስትና ግዴታ በማስገባት ጭምር ነው የተጠሪዎች ክርክር ተቀባይነት ቢያገኙ አመልካች መብት የሚያጣው በተበደሪው ላይ ብቻ ሳይሆን በዋሶቹ ላይ ጭምር ነው ይህም ማለት ደግሞ ስለብድሩ አመላለስ ጥንቃቄ በማድረግ ያደረገው ውል ዋጋ አጣበት ማለት ነው ይህ ሁሉ እየሆነ ያለውም እሱ /አመልካች/ ስምምነቱ ባልሰጡበት ሁኔታ ነው በወቅቱ ሊቀመንበር የተባለ ግለሰብ የብድሩ ገንዘብ 1ኛ ተጠሪ ለ3ኛ ተጠሪ እንዲሰጥ መፍቀዱም እንደአመልካች ማህበር ስምምነት የሚቆጠር ወይም ውሉ ተሻሽሎአል ለማለት የሚያስችል አይደለም ክሱ የቀረበለት ፍ/ቤት ይህን መሰል ክርክር የሚቀበልበት የሕግ ምክንያት አልነበረም ይልቁንም ፍ/ቤቱ ውሉን ለማሻሻል እንደማይችል በፍ/ብ/ሕግ ቁ 1763 የተመለከተውን ድንጋጌ ተላልፎአል ነው ለማለት የሚቻለው ሲጠቃለል የሥር ፍ/ቤቶች በተጠሪዎች የቀረውን ክርክር የተቀበሉት ከብድር ውሉ እና ከሕጉ ውጪ በሆነ ሁኔታ ነው ለማለት ችለናል፡፡

በመሆኑም አቤቱታ የቀረበበት ውሣኔ በሕጉ አተረጓጎም ረገድ መሠረታዊ ስህተት የተፈጸመበት ነው ብለናል መከፈል ያለበት የገንዘብ መጠን በሚመለከት የቀረበው የአመልካች አቤቱታ ግን የምንለውጥበት በቂ ምክንያት ባለማግኘታችን አልፈነዋል፡፡

 

 

   

 

1.            የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ.ቁ 74893 መጋቢት 27 ቀን 99 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔ እና የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ.ቁ 55349 ጥር 20 ቀን 2001 የሰጠው ፍርድ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁ 348/1/ መሠረት ተሻሽለዋል፡፡

2.            ከአመልካች ጋር በተደረገው የብድር ውል ተበዳሪው 1ኛ ተጠሪ ነው ብለናል ከ2 እስከ 4 የተጠቀሱት ተጠሪዎችንም የአንድነትና የነጠላ የዋስትና የገቡ ናቸው በዚህ መሠረትም 1ኛ ተጠሪ እና ከ2 እስከ 4 የተጠቀሱት ተጠሪዎች በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የተወሰነውን ብር 6424.76 /ስድስት ሺህ አራት መቶ ሃያ አራት ብር ከሰባ ስድስት ሣንቲም/ በአንድነት እና በነጠላ እንዲከፈሉ ወስነናል፡፡ ዕዳው ተከፍሎ አለቀ ድረስም ወለድ 9% /ዘጠኝ በመቶ/ ይታሰብ ብለናል፡፡

3.            5ኛ ተጠሪ በገባው የጠለፋ ዋስትና ውል መሠረት ግዴታውን ሊወጣ ይገባል ብለናል፡፡

4.            ግራቀኙ ወገኖች ወጪና ኪሣራቸው ይቻሉ

መዝገቡ ተዘግቶአል፡፡ ይመለስ፡፡  

       የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት

 

ም.አ

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

No comments:

Post a Comment

Cancellation of Contracts

   Cancellation of Contracts Cancellation is another remedy for non-performance. Cancellation brings an already existing contract to an end....