Wednesday, September 9, 2020

የኪራይ ውል-ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የሀላፊነት ወሰን- ሰ/መ/ቁ. 34155

 የሰ/መ/ቁ. 34155

ኀዳር ዐ4/2ዐዐ1

ዳኞች፡- አብዱልቃድር መሐመድ

      ታፈሰ ይርጋ

      ፀጋዬ አስማማው

 አልማው ወሌ

      ዓሊ መሐመድ

አመልካቾች፡- 1/ ኢንጂነር ቀለሙ ስንቄ ጠበቃ ብስራት መኮንን ቀርበዋል፡፡

           2/ ከበደ ሚካኤል አካዳሚ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር “    

ተጠሪ፡- ኢንጂነር ሳቲኖ ማስካሮ - ጠበቃ ቴዎድሮስ ሃ/ስላሴ ቀርበዋል፡፡

     ጉዳዩ ለምርመራ በተቀጠረው መሠረት ተመርምሮ የሚከተለውን ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

ፍ ር ድ

     አቤቱታው የቀረበው የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በኮ/ቁ. 28ዐ46፣ ጥር 3ዐ/1998 ዓ.ም. የሰጠውን ፍርድ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በይግባኝ አይቶ ካከራከረ በኋላ በፍ/ይ/መ/ቁ. 23732፣ ኀዳር ዐ6/2ዐዐዐ ዓ.ም. በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 348/1/ በማጽናቱ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ፈጽሟል በሚል ነው፡፡

     የአሁኑ አመልካቾች በስር ፍርድ ቤቱ ተከሣሾች፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ ባዮች የነበሩ ሲሆን የአሁኑ ተጠሪ ደግሞ በሥር ፍርድ ቤቱ ከሣሽ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ደግሞ መልስ ሰጭ በመሆን የተከራከሩ ሲሆን ስር ከሣሽ ጥር 13 ቀን 1996 ዓ.ም. ወደ ሥር ፍርድ ቤቱ ያቀረቡት ክስ መሠረታዊ ይዘቱ ከ1ኛ ተከሣሽ በጋራ በመሆን ከበደ ሚካኤል አካዳሚ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር ስንመሰርት ተቋሙ ስራውን የሚያከናውነው በአዲስ አበባ ከተማ፣ ወረዳ 17፣ ቀበሌ 2ዐ፣ የቤት ቁጥር 755 በሆነው በ124ዐ ካ.ሜ. በታነፀው የከሣሽ ባለሁለት ፎቅ ሕንፃ ውስጥ በመሆኑ ለዚሁ አገልግሎት ወደፊት በገበያ ዋጋ በምንተምነው የኪራይ ሂሣብ ለከሣሽ እንደሚከፈል የቃል ስምምነት ያደረግን ሲሆን ማኀበሩም ተመስርቶ በዚሁ ሕንፃዬ የትምህርት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፤ ይሁን እንጂ 1ኛ ተከሣሽ የሕንፃው ኪሣይ ለከሣሽ ለመክፈል ፈቃደኛ ባለመሆኑ ጉዳዩን በሽምግልና ለመጨረስ በወሰነው መሠረት ሽማግሌዎች ለሕንፃው በወር ብር 45ዐዐዐ /አርባ አምስት ሺህ ብር/ ተከሣሹ እንዲከፍለኝ አስማምተውን ሲያበቁ ለመክፈል ፈቃኛ አልሆነም፤ ስለሆነም ትምህርት ቤቱ በቤቱ መገልገል ከጀመረበት ከሰኔ 21/1992 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሰኔ 3ዐ/1995 ዓ.ም. ያለውን የቤት ኪራይ ሽማግሌዎቹ በተመኑት ወርሃዊ ኪራይ ብር 45ዐዐዐ /አርባ አምስት ሺህ ብር/ ሂሣብ ታስቦ ከነ ወለዱ፤ የዳኝነት የጠበቃ አበል 1ዐ% እና ወጪና ኪሣራ ታስቦ ይከፈለኝ የሚል ነው፡፡

     ስር ተከሣሾችም በበኩላቸው መጋቢት ዐ8/1996 ዓ.ም. በተፃፈ መልስ የሰጡ ሲሆን ይዘቱም በከሣሽ የተጠቀሰው ሕንፃ የከሣሽ መሆኑ እሙን ሆኖ የትምህርት ስራችን በዚሁ ሕንፃ ለማከናወን ከሣሽ በነፃ ፈቅደው ያስመዘገቡ እንጂ የኪራዩን ተመን በገበያ ዋጋ ወደፊት ለመክፈል ተከሣሽ አልተሰማማም፤ አለ እንኳ ቢባል ወደፊት የኪራይ ውል ለመግባት የሚሰጥ ቃል በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1675፣ 1678፣ 1679፣ 168ዐ እና 2896 መሠረት የኪራይ ውል ሊባል ስለማይችል ተቀባይነት የለውም፤ ከሣሽ በሕንፃቸው ውስጥ ስራችን እንድናከናውን የፈቀዱት ትምህርት ቤቱ ስራውን ከመጀመሩ በፊት የከሣሽ ሕንፃ ያላለቀና ገና ጅምር ሕንፃ በመኖሩ 1ኛ ተከሣሽ የግል ገንዘቤ የሆነውን ብር 6ዐዐ,ዐዐዐ /ስድስት መቶ ሺህ ብር/ አውጥተው እንዲጠቃለል በማድረጌና ጊዜዬና እውቀቴ ለግንባታው በማዋሌ ነው፡፡ እኔ ለሕንፃው በወር ብር 45ዐዐዐ /አርባ አምስት ሺህ ብር/ ለከሣሽ እንድከፍል ሽማግሌዎች አልወሰዱም ቢወስኑም በእኔ ላይ አስገዳጅነት የለውም፤ ከሣሽ ከ2ኛ ተከሣሽ ውስጥ ባለ ሽርክና በመሆናቸው እርሳቸውም አብረው ሊከሰሱ ይገባቸዋል፤ ሰለሆነም አላግባብ የመሠረቱት ክስ ውድቅ በማድረግ ወጪና ኪሣራ ይወሰንልን የሚል ነው፡፡

     የሥር ፍ/ቤትም የግራ ቀኙ ወገኖች ክርክር ከሰውና ጽሁፍ ማስረጃዎች ጋር ካገናዘበ በኋላ በሰጠው ፍርድ ከሣሽ በድርጅቱ ውስጥ ሽርክና ያለው በመሆኑ በተከሣሽነት አብሮ መግባት አለበት የሚለውን የ1ኛ ተከሣሽ ክርክር ተቀባይነት የለውም፤ ከመስከረም 1/1995 ዓ.ም. ጀምሮ 1ኛ ተከሣሽ ለከሣሽ የቤቱን ኪራይ ለመክፈል እንደተስማሙ በምስክሮች በመረጋገጡ እስከ ሰኔ 3ዐ/1995 ዓ.ም. ድረስ ያለውን ኪራይ በወር ብር 45ዐዐዐ ብር /አርባ አምስት ሺህ ብር/ ሒሣብ ማለትም 45ዐዐዐx በ1ዐ ወራት ብር 45ዐ,ዐዐዐ /አራት መቶ ሃምሣ ሺህ ብር/ እንዲሁም ከ2/6/96 ዓ.ም. ጀምሮ 9% ወለድ ጨምረው ተከሳሾቹ በአንድነትና በነጠላ ለከሣሽ እንዲከፍሉ ብሏል፡፡

     የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትም በሁለቱ ስር ተከሳሾች የቀረበለትን ይግባኝ ካከራከረ በኋላ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 348/1/ መሠረት የስር ፍርድ ቤቱን ውሣኔ አጽንቷል፡፡

     ከላይ የተቀመጠውን ፍርድ በመቃወም የአሁኑ አመልካቾች ኀዳር 27/2ዐዐዐ ዓ.ም. በተፃፈ ማመልከቻ ቅሬታ አቅርበዋል፤ አጭር ይዘቱም በአመልካቾችና በተጠሪ መካከል የቤት ኪራይ ውል የለም፤ የስር ፍርድ ቤቱ አስቀርቦ የሰማቸው ምስክሮች በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 3318-3324 መሠረት አስታራቂዎች እንጂ በፍ/ሕ/ቁ. 3325-3346 መሠረት ውሣኔ ለመስጠት የተሰየሙ የግልግል ዳኞች አለመሆናቸውን ባለመገንዘብና በግልግል ዳኛና በአስታራቂ ሽማግሌ መካከል ያለውን ከፍተኛ ልዩነት በሚገባ ባለመረዳት የተሰጠ ውሣኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ነው የኪራይ ውል አለ ቢባል እንኳ ለድርጅቱ ጥቅም እስከሆነ ድረስ 1ኛ አመልካች ተጠያቂ የሚሆንበት ምክንያት የለም፤ የሚጠየቅ ከሆነ ተጠሪ በሽርክና የሚገኙበት 2ኛ አመልካች እንጂ 1ኛ አመልካች አይደለም የሚል ነው፡፡

     ተጠሪም ሚያዝያ 24/2ዐዐዐ ዓ.ም. በተፃፈ መልሣቸው በአመልካችና በተጠሪ መካከል ውል መኖሩን ለማረጋገጥ የሰው ምስክር አቀረብኩ እንጂ ጽሁፍ አለኝ ብዬ አልተከራከርኩም፤ አስታራቂ ሽማግሌዎች አዘጋጅተው ያቀረቡትን ጽሑፍ 1ኛ አመልካች ለመፈረም ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ለማሳየት ያቀረብኩት የጽሁፍ ማስረጃ እንጂ የመጨረሻ አስገዳጅነት ያለው ጽሁፍ በማለት ማስረጃውን አላቀረቡም በማለት የስር ፍርድ ቤቶቹ የፈፀሙት መሠረታዊ የሕግ ስህተት እንደለ በመግለጽ ውሣኔው እንዲፀና ጠይቀዋል፡፡

     አመልካቾችም ግንቦት 14/2ዐዐዐ ዓ.ም. በተፃፈ የመልስ መልስ የሰጡ ሲሆን ይዘቱም በአመልካችና በተጠሪ መካከል የተደረገ የጽሁፍ ውል እንደሌለ ተጠሪም ስላመኑ እንዲሁም አስገዳጅ የሆነ የአስታራቂ ሽማግሌዎች ሂደት በመካከላችን ስለሌለ የስር ፍርድ ቤት ውሣኔ ውድቅ ሊሆን ይገባል የሚል ነው፡፡

     በሰበር ችሎቱም የግራ ቀኙ ወገኖች ክርክር አመጣጥ ከላይ እየተዘረዘረ በመጣው መልኩ በመገንዘብ የ1ኛ አመልካችና የተጠሪ የጋራ ሃብት የሆነው የራሱ ሕጋዊ ሰውነት ያለው 2ኛው አመልካች ለተገለገለበት የተጠሪ ሕንፃ 1ኛ አመልካች በግላቸው ኃላፊነት አለባቸው ሊባሉ ይገባል ወይስ አይገባም? የሚለውን መሠረታዊ ጭብጥ በማስቀመጥ ጉዳዩን እንደሚከተለው ተንትኗል፡፡

     ከክርክሩ ለመገንዘብ እንደተቻለው 2ኛው አመልካች ማለትም ከበደ ሚካኤል አካደሚ ኃላ/የተ/የግል ማኀበር በ1ኛ አመልካችና በተጠሪው መካከል በተደረገ የሽርክና ውል የተቋቋመ ኃላፊነቱ የተወሰነ በትምህርት ዘርፍ የተሰማራ የንግድ ተቋም ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ መስራቾቹ በተቋሙ ውስጥ ባላቸው የአክሲዮን ድረሻ መሠረት አድርገው ገቢን እንደሚካፈሉና በድርጅቱ ስም የመጣ ኃላፊነት ወይም እዳ ቢኖር ወደ መስራቾቹ የግል ሃብት መሄድ ሳያስፈልግ በተቋሙ ሃብት ብቻ ታጥሮ ተፈፃሚ የሚሆንበት የማኀደር አይነት ነው፡፡ ግራ ቀኙ ወገኖች እያካሄዱት ወዳለው ክርክር ሲመጣ ደግሞ የስር ከሣሽ የአሁኑ ተጠሪ ጥያቄ ከበደ ሚካኤል አካዳሚ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኀበር ትምህርታዊ አገልግሎት የሚሰጠው የተጠሪን ሕንፃ በመጠቀም መሆኑ 1ኛ አመልካችም ሆነ ተጠሪ ያልተካካዱበት ጉዳይ ሆኖ የ1ኛ አመልካች ቁልፍ ክርክር በሕንፃው ወርሃዊ ኪራይ በግሌ የተለየ ግዴታ የለብኝም የሚል ነው፣ ተጠሪ የሕንፃው ኪራይ በ1ኛ አመልካች የግል ሃብት /ማለትም ከሽርክና ተቋሙ ውጭ ባላቸው ሌላ ሃብት/ ተፈፃሚ ለማድረግ የሚያስችል በሕግ የሚፀና ውል አላቀረቡም፤ ላቀረቡት ክስ በዋና ማስረጃነት በክርክሩ የተመለከተው የሰው ምስክሮች ቀርበው ለፍርድ ቤቱ የሰጡት ምስክርነት ሲሆን የዚህ አጠቃላይ ይዘት ሲታይም 2ኛ አመልካች ለሚሰጠው ግልጋሎት የተጠሪን ሕንፃ በመጠቀም በመሆኑ ተጠሪው ለዚሁ ንብረታቸው ኪራይ እንዲታሰብላቸው 1ኛ አመልካችና ተጠሪን እንዲግባቧቸው ነው፤ 2ኛ አመልካችም ሕንፃውን እንደተጠቀመ ነው፡፡ ስለሆነም የሕንፃው ኪራይ እዳ ከ2ኛ አመልካች አልፎ ወደ 1ኛ አመልካች የሚተለለፍበት ሕጋዊ አግባብ ወይም የውል መሠረት ሳይኖር 1ኛ አመልካች በግላቸው ኃላፊነት አለባቸው በማለት የስር ፍርድ ቤቱ የሰጠው ትርጉም መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ ተገኝቷል፡፡

ው ሣ ኔ

1.  የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በኮ/መ/ቁ. 28ዐ46 ጥር 3ዐ/1998 ዓ.ም. የሰጠው ፍርድ እንዲሁም የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በፍ/ይ/መ/ቁ. 23732 ኀዳር ዐ6/2ዐዐዐ ዓ.ም. የሰጠው ፍርድ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 348/1/ መሠረት ተሻሽለዋል፤ ይፃፍ፡፡

2.  2ኛ አመልካች የሆነው ከበደ ሚካኤል አካዳሚ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኀበር በሕግ የተቋቋመበትን ትምህርታዊ አገልግሎት በተጠሪ ሕንፃ መሰጠቱ ስለተረጋገጠና ለዚሁ ግልጋሎትም ከመስከረም 1/1995 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 3ዐ/1995 ዓ.ም. በወር ብር 45ዐዐዐ /አርባ አምስት ሺህ ብር/ ሒሣብ ከተጠሪ ለመከራየት በ1ኛ አመልካች በኩል መስማማቱ በቀረቡት ማስረጃዎች በመረጋገጡ ጠቅላላ ብር 45ዐ,ዐዐዐ /አራት ዓመት ሃምሣ ሺህ ብር/ ለተጠሪ ይክፈል፤ እንዲሁም ከየካቲት ዐ2/1996 ዓ.ም. ጀምሮ ይህ ገንዘብ ተከፍሎ እስኪያልቅ 9% ወለድ ጨምሮ ይክፈል፤ ተጠሪ በዚህ ክርክር ለከፈሉት የዳኝነት ገንዘብ 2ኛ ተጠሪ ይክፈል፤ ወጪና ኪሣራ በተመለከተም ዝርዝር የማቅረብ መብት ተጠብቆላቸዋል፡፡

3.  1ኛ አመልካች ከተጠሪ ሕንፃ በግላቸው የገቡት ውል ባለመኖሩ ከ2ኛ አመልካች ጋር በጋራና በነጠላ ሆነው የሕንፃው ኪራይ የመክፈል ግዴታ የላቸውም፡፡

4.  ግራ ቀኙ ወገኖች በዚህ የሰበር ችሎት ያወጡትን ወጪና ኪሣራ በሚመለከት ይቻቻሉ ብለናል፡፡

ጉዳዩ ያለቀ በመሆኑ መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

ነ/ዓ

1 comment:

Cancellation of Contracts

   Cancellation of Contracts Cancellation is another remedy for non-performance. Cancellation brings an already existing contract to an end....