Sunday, March 7, 2021

ወ/ሮ ሽብሬ መኩሪያ እና እነ ወ/ሮ ደሜ ጅሩ /2 ሰዎች/ ሰ/መ/ቁ 48126 ይርጋ

 

የሰበር መ/ቁ 48126

የካቲት 3 ቀን 2002 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- መንበረፀሐይ ታደሰ

        ሐጐስ ወልዱ

        ሂሩት መለሰ

        ብርሃኑ አመነው

        አልማው ወሌ

 

አመልካች፡- ወ/ሮ ሽብሬ መኩሪያ ቀረበች

ተጠሪዎች፡- 1. ወ/ሮ ደሜ ጅሩ

           2. ሞያ ረታ ቀረበ

      መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

ፍ ር ድ

      ለአቤቱታው መነሻ የሆነው ጉዳይ ያለአግባብ የተያዘ መሬት ይለቀቅልኝ በሚል የቀረበውን ክስ የሚመለከት ነው፡፡ ክርክሩ የተጀመረው በአርሲ ዞን በሊሙና ቢልቢሎ ወረዳ ፍ/ቤት ሆኖ ከሣሽ የነበረችውም አመልካች ናት፡፡ አመልካች በተጠሪዎች ላይ ክስ የመሠረተችው ለጊዜው እንዲጠቀሙበት ሰጥቻቸው የነበረው መሬት ሊመልሱልኝ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው እንዲመልሱ ይገደዱልኝ በማለት ነው፡፡ ተጠሪዎች ደግሞ መሬቱ የተሰጠን እንድንመልስ ሳይሆን በዘለቄታ ነው፡፡ የስጦታ ውሉም አልፈረሰም፡፡ ቋሚ ተክል በመትከል ከአሥራ አንድ ዓመት በላይ ይዘን እየተጠቀምንበት በመሆኑ የምንለቅበት አግባብ የለም በማለት የተከራከሩ ሲሆን፣ ፍ/ቤቱም የሁለቱን ወገኖች ክርክር ከመረመረ በኋላ ክሱ በይርጋ ቀሪ ሆኖአል በማለት የአመልካችን ጥያቄ ውድቅ አድርጎአል፡፡ በዚህ ውሳኔ ላይ ይግባኝ የቀረበላቸው የአርሲ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት እና የኦሮሚያ ጠ/ፍ/ቤትም በወረዳው ፍ/ቤት የተሰጠው ውሳኔ ጉድለት የለበትም ብለዋል፡፡ የሰበር አቤቱታው የቀረበው በዚህ ላይ ነው፡፡

      እኛም አመልካች ነሐሴ 7 ቀን 2001 ዓ.ም በጻፈችው ማመልከቻ ያቀረበችውን አቤቱታ መሠረት በማድረግ ተጠሪዎችን አስቀርበን ክርክሩን ሰምተናል፡፡ ክርክሩ የተሰማው የሥር ፍ/ቤቶች የአመልካችን ክስ በይርጋ ቀሪ ነው ያሉት በአግባቡ ነው ወይስ አይደለም? በሚለው ጭብጥ ላይ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ረገድ ግራቀኝ ወገኖች ያሰሙት ክርክር አቤቱታ ከቀረበበት ውሳኔ እና ከሕጉ ጋር አገናዝበን መርምረናል፡፡

      ቀደም ሲል እንደተመለከተው ክርክሩ የተጀመረው በወረዳ ፍ/ቤት ነው፡፡ ፍ/ቤቱ የሰጠው ውሳኔ ከመዝገቡ ጋር ተያይዞ በመቅረቡ ተመልክተነዋል፡፡ ፍ/ቤቱ በውሳኔው ትችት ላይ በአመልካች እና በተጠሪዎች መካከል የስጦታ ውል እንዳለ እና ውሉም በሕግ አግባብ እንዳልፈረሰ ወይም እንዲፈርስ በሕጉ በተወሰነው የጊዜ ገደብ ውስጥ ክሱ እንዳልቀረበ ጠቅሶአል፡፡ በመጨረሻም ክሱ የቀረበው መሬቱ በተጠሪዎች ከተያዘ ከአሥር ዓመት በላይ ቆይቶ በመሆኑ በዚህ ረገድ የቀረበው የይርጋ መቃወሚያ ተቀባይነት ያለው ነው እሚል ትችት በውሳኔው ማጠቃለያ ላይ እንዳስቀመጠ ተመልክተናል፡፡ በእርግጥ አመልካች ፍ/ቤቱ የይርጋ መቃወሚያ ሳይቀርብለት ነው ብይኑ የሰጠው የሚል አቤቱታ በማመልከቻዋ ላይ አቅርባለች፡፡ ተጠሪዎች ደግሞ ክሱ በይርጋ ቀሪ ሆኖአል በማለት ስለመከራከራቸው በሰጡት መልስ የገለጹ ሲሆን፣ አመልካች ፍ/ቤቱ በራሱ ተነሳሽነት ስላለማንሳቱ ተጠሪዎች  ለሰበር ችሎቱ አላስረዱም በማለት በመልስ መልስዋ ከመግለጽ ውጪ ያቀረበችው አሳማኝ ክርክር የለም፡፡

      ተጠሪዎች መሬቱን የያዙት በ12-11-90 ዓ.ም በተደረገው ውል እንደሆነ በአመልካች የሰበር አቤቱታ በግልጽ ተመልክቶአል፡፡ ክሱ የተመሠረተው በ3-2-2001 ዓ.ም እንደሆነም እንደዚሁ በማመልከቻው ላይ የተገለጸ ሲሆን፣ ተጠሪዎች ደግሞ በውሉ መሠረት መሬቱን ተረክበው የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን በላዩ ላይ አፍርተው እየተጠቀሙበት እንደሆነ በመግለጽ መልስ ሰጥተው ተከራክረዋል፡፡ ክሱን የሰማው ፍ/ቤትም የተለያዩ ትችቶችን በውሳኔው ላይ ቢያስቀምጥም፤ በመጨረሻ ክርክሩን የቋጨው ግን ክሱ በይርጋ ቀሪ ሆኖአል በሚል ነው፡፡ የይርጋ መቃወሚያ በተጠሪዎች የተነሣ እንደሆነም በብይኑ ላይ አመልክቶአል፡፡ በዚህ መልክ በግልጽ የተቀመጠውን እውነታ አልተባለም የምንልበት አግባብ የለም፡፡ በመሆኑም በይርጋው አወሳሰን ረገድ የተፈጸመ መሠረታዊ የሕግ ስህተት አለ ለማለት አልቻልንም፡፡

ው ሳ ኔ

1.   በአርሲ ዞን የሌሙና ቢልቢሎ ወረዳ ፍ/ቤት በመ.ቁ 09/69 ግንቦት 4 ቀን 2001 ዓ.ም የሰጠው ብይን፣ የአርሲ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ.ቁ 20152 ግንቦት 9 ቀን 2001 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ እና የኦሮሚያ ጠ/ፍ/ቤት በመ.ቁ 81219 ሰኔ 10 ቀን 2001 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁ 348(1) መሠረት ፀንተዋል፡፡

2.   የአመልካች የሰበር አቤቱታ ተቀባይነት የለውም ብለናል፡፡

3.   በዚህ ሰበር ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሣራ ግራቀኝ ወገኖች የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡

መዝገቡ ተዘግቶአል፡፡ ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

ራ/ታ

No comments:

Post a Comment

Cancellation of Contracts

   Cancellation of Contracts Cancellation is another remedy for non-performance. Cancellation brings an already existing contract to an end....