Monday, March 8, 2021

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና እነ አቶ ናስር አባጊዳ አባገሮ /4 ሰዎች/ ሰ/መ/ቁጥር 48858 ብድር- እንደተከፈለ የሚቆጠር ክፍያ

 

                                                የሰ/መ/ቁጥር 48858

የካቲት 12 ቀን 2002 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- 1. ተገኔ ጌታነህ

        2. ሐጎስ ወልዱ

        3. ሂሩት መለሰ

        4. ብርሃኑ አመነው

        5. አልማው ወሌ

 

አመልካች፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ - ነ/ፈጅ ዳንኤል ጅፋር ቀረቡ

ተጠሪ፡- 1. አቶ ናስር አባጊዳ አባገሮ - አልቀረቡም

        2. ወ/ሮ አሚና ሐጂ አበፎጊ

        3. አቶ ሙሂድን አባ መጫ    በሌሉበት የሚታይ

        4. ወ/ሮ አምበሩ አባ ፊጣ

 

      መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

ፍ ር ድ

      በዚህ መዝገብ የቀረበው ጉዳይ በብድር የተሠጠን ገንዘብ የመክፈያ ጊዜ ጋር በተያያዘ የወለድ ዕዳው እንደተከፈለ ሊቆጠር የሚችልበትን የሕግ አግባብና ትርጉም የሚመለከት ነው፡፡

      ክርክሩ የተጀመረው በጅማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲሆን ከሣሽ የነበረው የአሁኑ አመልካች ባቀረበው የክስ አቤቱታ የአሁኑ አንደኛና ሁለተኛ ተጠሪዎች ታህሳስ 17 ቀን 1987 ዓ.ም በተፃፈ የብድር ውል ብር 30,000.00(ሰላሳ ሺህ) የተበደሩ መሆኑን፣ ሦስተኛ እና አራተኛ ተጠሪዎች ለዚሁ የገንዘብ መጠን የአንድነትና የነጠላ ዋስ በመሆን መፈረማቸውን፣ የዋናውን ብር ወለድና ልዩ ልዩ ወጪዎችን ጨምሮ ብር 14711.60(አስራ አራት ሺህ ሰባት መቶ አስራ አንድ ብር ከስልሳ ሳንቲም) ሊከፈሉ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን በመግለፅ ይህንኑ ገንዘብ እዳቸው ተከፍሎ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከሚታሰብ ወለድ እና የመቀጫ ወለድ፣ እንዲሁም ከሌሎች ወጪዎችና ኪሳራዎች ጋር ተጠሪዎች ባልተነጣጣለ ኃላፊነት እንዲከፍሉ ይወሰንለት ዘንድ ዳኝነት ጠይቋል፡፡

      1ኛ ተጠሪ ቀርበው ብድሩን መውሰዳቸውን አምነው ክሱ ከአስር አመት በኋላ የቀረበ በመሆኑ በይርጋ እንዲታገድ፣ በጥር 29 ቀን 1991 ዓ.ም የተፃፈ ደብዳቤ የማያውቁት መሆኑን በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያነት በፍሬ ነገር ረገድም ወለድ በሁለት ዓመት ውስጥ ካልተከፈለ እንደተከፈለ ስለሚቆጠር የተጠራቀመውን ወለድ የሚከፍሉበት አግባብ የሌለ መሆኑን፣ በብድር ከወሰዱት ገንዘብ ውስጥ ብር 29900.00(ሃያ ዘጠኝ ሺህ ዘጠኝ መቶ) ከፍለው ብር 100.00 ብቻ እንደሚቀርባቸው ገልጸው ክሱ ውድቅ ሊሆን ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ ሌሎች ተጠሪዎች ያቀረቡት ክርክር የለም፡፡ ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም ክርክሩን ከመረመረ እና የ1ኛ ተጠሪን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ውድቅ ከአደረገ በኋላ ተጠሪዎችን የተጠራቀመውን ወለድ የመክፈል ኃላፊነት አለባቸው ወይስ የለባቸውም? የሚለውን ጭብጥ መስርቶ ጉዳዩን በመመርመር አመልካች ለ1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች የሠጠው ብድር ወለድ አለመከፈሉ የታመነ ጉዳይ ስለሆነ በፍ/ሕ/ቁጥር 2024(ረ) መሠረት አበዳሪው የተወሠነ ጊዜ ተበጅቶለት በዓመት ወይም ከዓመት በፊት የሚከፈለውን የገንዘብ ዕዳ ሣይጠይቅ እስከ ሁለት ዓመት ጊዜ ከቆየና ከሁለት ዓመት ጊዜ በኋላ ከጠየቀ ገንዘቡ በተበዳሪው እንደተከፈለ ወይም ዕዳው ምህረት እንደተደረገለት ሕግ ግምት የሚወስደው፤ ገንዘቡ በጊዜ ማለፍ እንደተከፈለ የሚቆጠረው ባለዕዳው እዳውን በፁሑፍ ባመነበት ሁኔታ አይደለም የሚለውን ምክንያት በመያዝ ወለድን በተመለከተ ተጠሪዎች በአንድነት እና በነጠላ እንዲከፍሉ ሲል ወስኗል፡፡

1ኛ ተጠሪ በዚሁ ውሣኔ ባለመስማማት ይግባኙን ለኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅርበው ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ተሽሮ የወለድ ገንዘቡ በሁለት ዓመት የጊዜ ማለፍ ምክንያት እንደተከፈለ ይቆጠራል ለወለድ የታሰበው ተቀንሶ ተጠሪዎች ብር 8273.50 ተከፍሎ እስኪጠናቀቅ ከሚታሰብ 9% (ዘጠኝ ከመቶ) ጋር በአንድነት እና በነጠላ እንዲከፍሉ ተብሎ በአብላጫ ድምፅ ተሻሽሎ ተወስኗል፡፡ የአሁኑ የሠበር አቤቱታ የቀረበውም በዚሁ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በሠጠው ውሳኔ ላይ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል በማለት ለማስቀየር ነው፡፡

      የአመልካች ነገረ ፈጅ ጳጉሜ 03 ቀን 2001 ዓ.ም በፃፉት ሶስት ገፅ የሰበር አቤቱታ በበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል የሚሉበትን ምክንያት ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡ ይዘቱም ባጭሩ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለጉዳዩ መሠረት ያደረገው ድንጋጌ የፍ/ህ/ቁጥር 2024 ለጉዳዩ ተፈፃሚነት የሌለው መሆኑን በመጥቀስ ውሣኔው መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ነው ተብሎ ተሽሮ ተጠሪዎች በሥር ፍርድ ቤት በቀረበባቸው ክስ መሠረት በብድር ዕዳ የሚፈለግባቸውን የወለድ እዳ ከክርክሩ ወጪና ኪሣራ ጋር በአንድነትና በነጠላ እንዲከፍሉ ይወሰንለት ዘንድ ዳኝነት መጠየቁን የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ የሠበር ሠሚ ችሎትም አመልካች በሥር ፍርድ ቤት ያቀረበው የወለድ ይከፈለኝ ክስ በፍ/ሕ/ቁጥር 2024(ረ) መሰረት እንደተከፈለ ይቆጠራል በሚል ውድቅ እንዲሆን የመወሰኑን አግባብነት ለመመርመር አቤቱታው ለሠበር ችሎት ቀርቦ እንዲታይ አድርጓል፡፡

      ለተጠሪዎች ጥሪ ተደርጎላቸው ከ2ኛ እስከ 4ኛ ተራ ያሉት ተጠሪዎች ያልቀረቡ ሲሆን 1ኛ ተጠሪ ቀርበው ታህሳስ 22 ቀን 2002 ዓ.ም በተጻፈ አንድ ገፅ ማመልከቻ መልሳቸውን ሰጠተዋል፡፡ ይዘቱም ባጭሩ የፍ/ህ/ቁጥር 2024(ረ) ለጉዳዩ አግባብነት ያለው መሆኑን በ29/5/1991 ዓ.ም ተጻፈ የተባለው መረጃም ተጠሪ ያልጻፉትና በፍላጎታቸው ያልተገኘ መሆኑን ዘርዝረው የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ሊፀና ይገባል በማለት የተከራከሩ ስለመሆኑ የሚያሣይ ነው፡፡

      የጉዳዩ አመጣጥ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የቀረበውን ክርክር ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ቀርቦ ሊታይ ይገባዋል ሲባል ከተያዘው ጭብጥ አኳያ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡

ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አመልካች በአሁኑ ተጠሪዎች ላይ ያቀረበውን ክስ የብድር ዕዳው አለመከፈሉን አረጋግጦ ወለድን በተመለከተ ብቻ በጊዜ ማለፍ ግምት እንደተከፈለ በመቁጠር ተጠሪዎችን ነጻ ማድረጉን ነው፡፡

      የዚህን ችሎት ምላሽ የሚያስፈልገው ዋናው ነጥብ አመልካች ያቀረበው የዋናው ብድር ወለድ ይከፈለኝ ጥያቄ በፍ/ብ/ህ/ቁጥር 2024(ረ) መሰረት በሁለት ዓመት የጊዜ ማለፍ እንደተከፈለ ይቆጠራል በሚል የሕግ ግምት ይሸፈናል ተብሎ የአመልካች ማስተባበያ ማስረጃ ሳይመረመር መወሰኑ ባግባቡ ነውን? የሚለው ነው፡፡

      ይህ ችሎት በመ/ቁጥር 29181 አግባብነት ያላቸውን የፍትሐብሔር ሕግ ድነጋጌዎች በመተርጎም የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2026(1) ለባንኮችና ለደንበኞቻቸው መብት ልዩ ጥበቃ የሚያደርገውን የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2473(2) ድንጋጌ ዋጋ በሚያሳጣ መንገድ ሊተረጎምና ተፈፃሚ መሆን እንደማይገባ፣ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2026(1) ድንጋጌ በባንኮችና በሌሎች አበዳሪ ተቋማት እና ደንበኞቻቸው መካከል ያለውን ግንኙነት በተመለከተ ተፈፃሚነት የሌለው የህግ ድንጋጌ መሆኑን በመተንተን ባንኮች ለደንበኞቻቸው ያበደሩትን የብድር ወለድ ያልተከፈለ መሆኑን በሰው ምስክር፣ የሰነድና ሌላ ማስረጃ በማቅረብ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2024(ረ) ስር የተደነገገውን የሕሊና ግምት ለማስተባበል የሚችሉ መሆኑን በመግለፅ አስገዳጅ የሆነ የሕግ ትርጉም ሰጥቶበታል፡፡ በዚህ የሕግ ትርጉም መሰረት በዚህ ጉዳይ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ለውሳኔው መሰረት ያደረገው ምክንያት አግባብነትና ተፈፃሚነት ያለውን ሕግ ባለመሆኑ ውሳኔው መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ አግኝተናል፡፡

      በስር ፍርድ ቤት በዋና ተበዳሪነት የተከሰሱት የአሁኑ 1ኛ ተጠሪ በዚህ ችሎትም ሆነ በስር ፍርድ ቤት በሠጡት መልስ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2024(ረ) ለጉዳዩ አግባብነት አለው በማለት መከራከራቸውን ተገንዝበናል፡፡ ይሁን እንጂ በክርክሩ ሂደት ለክሱ መነሻ የሆነው ገንዘብ ለአመልካች ያልተከፈለው መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ዕዳው ያልተከፈለ ስለመሆኑ የፃፉትን ደብዳቤም ከፍላጎቴ ውጪ ነው የተገኘው ከሚሉ በስተቀር በኃይል ወይም በግዳጅ የተገኘ ስለመሆኑ በማስረጃ ያላረጋገጡ መሆኑን የስር ፍርድ ቤት በውሳኔው ላይ በግልፅ አስፍሯል፡፡ ስለሆነም ለአመልካች 1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች የተበደሩትንና ለክሱ መነሻ የሆነውን የብድር ወለድ ገንዘብ ያልከፈሉ ስለመሆኑ ስለተረጋገጠ 1ኛ ተጠሪ የማይከፍሉበትን ሕጋዊ ምክንያት አላገኘንም፡፡ ሌሎች ተጠሪዎችም በዚህ ችሎትም ሆነ በስር ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ሲሆን 1ኛ ተጠሪ ያቀረቧቸው የመከራከሪያ ነጥቦች ከኃላፊነት ነፃ የሚያደርጋቸው ሆኖ አላገኘንም፡፡ 3ኛ እና 4ኛ ተጠሪዎች የገቡት የዋስትና ዓይነት የአንድነትና የነጠላ እንደመሆኑ መጠን በገቡት ግዴታ መሰረት ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ገንዘብ ለአመልካች የማይከፍሉበትን ሕጋዊ ምክንያት አላገኘንም፡፡ ሲጠቃለልም ከላይ በተመለከቱት ምክንያቶች ተከታዩን ወስነናል፡፡

ው ሣ ኔ

  1. በኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 73563 ሰኔ 11 ቀን 2001 ዓ.ም የሠጠው ውሣኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሻሽሏል፡፡
  2. የጅማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 03727 ታህሳስ 23 ቀን 2001 ዓ.ም የሠጠው ውሣኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ሙሉ በሙሉ ፀንቷል፡፡
  3. በዚህ ችሎት በክርክሩ የወጡትን ሌሎች ወጪዎችንና ኪሳራዎችን የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

ራ/ታ

 

No comments:

Post a Comment

Cancellation of Contracts

   Cancellation of Contracts Cancellation is another remedy for non-performance. Cancellation brings an already existing contract to an end....