Tuesday, March 9, 2021

ጀኔራል ፓራሜድ ካል ኮሌጅ እና የሸቀጦች ጅምላ ንግድና አስመጪ ድርጅት ሰ/መ/ቁ 46130 ውዝፍ የኪራይ ገንዘብ

 

የሰ/መ/ቁ 46130

ጥር 26 ቀን 2002 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ

        ሐጐስ ወልዱ

        ሂሩት መለሰ

        ብርሃኑ አመነው

        አልማው ወሌ

 

አመልካች፡- ጀኔራል ፓራሜድ ካል ኮሌጅ - ጠ/ማንጉዳይ ወንድሙ ቀረቡ

ተጠሪ፡- የሸቀጦች ጅምላ ንግድና አስመጪ ድርጅት - ጠ/ተስፋዬ ቀለመወርቅ

      መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

ፍ ር ድ

      በዚህ መዝገብ የቀረበው ጉዳይ የቤት ኪራይ ገንዘብ የሚመለከት ነው፡፡ ተጠሪ በሥር ፍ/ቤት ባቀረበው ክስ ተጠሪው በውክልና የሚያስተዳድረውን የመንግስት የልማት ድርጅት ሕንፃ ክፍል አመልካች /ሥር ተከሳሽ/ ተከራይቶ እየተጠቀመበት መሆኑን ገልፆ ከ08/06/98፣ 12/6/98 እና 22/07/98 ዓ.ም ጀምሮ ክስ እስከቀረበበት 30/07/2000 ዓ.ም ያለውን ውዝፍ የኪራይ ገንዘብ ተጨማሪ እሴት ታክስን ጨምሮ ብር 156211.78 እንዲከፍል እንዲወሰን አመልክቷል፡፡

      በአመልካች በኩል የቀረበው ዋነኛ ክርክር የውዝፍ ኪራይ ገንዘብ ጥያቄ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ባለመጠየቁ በፍ/ብ/ህ/ቁ 2024/መ/ መሠረት እንደተከፈለ ይቆጠራል የሚል ነው፡፡

      ጉዳዩን በቀጥታ ክስ የተመለከተው የአዋሳ ከፍተኛ ፍ/ቤት በአመልካች እና በተጠሪ መካከል የተፃፃፉትን ደብዳቤዎች እና ለተጠሪ በ27/11/99 ዓ.ም አመልካች ካለበት እዳ ታሳቢ ብር 28000.00 (ሃይ ስምንት ሺህ) የከፈለበትን ደረሰኝ ተጠሪው ስላቀረበ ይህንኑ መሠረት በማድረግ ክርክሩን ውድቅ አድርጐ የሚፈለግበትን ቀሪ ገንዘብ እንዲከፍል ወስኗል፡፡

      በውሳኔው ቅር ተሰኝቶ የሥር ተከሳሽ (አመልካቹ) ለክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት እና ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ ያቀረበ ቢሆንም ተቀባይነት አላገኘም፡፡

      የአመልካች ጠበቃ ለዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት በ24/09/01 ዓ.ም ጽፈው ያቀረቡት አቤቱታ ይዘት በሥር ፍ/ቤት የተጠቀሱት ደብዳቤዎች የህሊና ግምት የሚያስቀሩ አለመሆኑን በአመልካች ተከፍሏል የተባለው ገንዘብም ክስ የቀረበበት ገንዘብ ሳይሆን ቀደም ብሎ ያለውን የሚመለከት ስለመሆኑ ጠቅሶ በፍ/ብ/ህ/ቁ 2024/መ/ መሠረት የህልና ግምት ተጠቃሚ እንደሆነ እንዲወሰን አመልክቷል፡፡

      ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት የአመልካችን አቤቱታ መርምሮ ጉዳዩ ከፍ/ብ/ህ/ቁ 2024/መ/ አንፃር ለመመርመር ተጠሪን አስቀርቦ ጥቅምት 19/2002 ዓ.ም በዋለው ችሎት ክርክራቸውን ሰምቷል፡፡

      በእኛም በኩል ከተያዘው ጭብጥ አንፃር ጉዳዩን ከሕጉ ጋር አገናዝበን መርምረናል፡፡

      እንደመረመርነውም የሕግ ግምት ተጠቃሚ ለመሆን በአመልካች በኩል የቀረበው መከራከሪያ የተፃፉት ደብዳቤዎችም ሆኑ የተከፈለው ደረሰኝ (ሰነድ) ባለመካድ መሆኑ እንዲሁም በ27/11/99 ዓ.ም የተከፈለው አሁን ለተጠየቀው ሳይሆን ቀድሞ ለነበረ የኪራይ ገንዘብ ነው ቢልም በሥር ፍ/ቤት ይህንን በተጨባጭ ማስረጃ ስለማረጋገጡ መዝገቡ ውስጥ አልተመለከተም፡፡

      ስለሆነም በሥር ፍ/ቤት በተረጋገጠው ፍሬ ነገር መሠረት አመልካች ያለበትን እዳ ለመክፈል ደብዳቤ መፃፉ እንዲሁም የህጉ ዓላማ ዳተኛ ባለገንዘብን ለመግታት እንጂ እንደአመልካች አቀራረብም በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ካለበት እዳ ብር 28000.00 መክፈሉ ሲታይ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2024/መ/ በመጥቀስ የቀረበውን ክርክር የሥር ፍ/ቤት አለመቀበሉ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ነው ለማለት አልተቻለም፡፡ ስለሆነም በሥር ፍ/ቤት የተሰጠው ውሳኔ ባለበት እንዲፀና ብለናል፡፡

ው ሳ ኔ

      የአዋሳ ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ 4900 የሰጠው ውሳኔ፣ የደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/ጠቅላይ ፍ/ቤት በመ/ቁ 26199 የሰጠው ትዕዛዝ እና የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁ 26546 የሰጠው ትዕዛዝ ፀንቷል፡፡

      ግራቀኙ የዚህን ፍ/ቤት ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

ራ/ታ

No comments:

Post a Comment

Cancellation of Contracts

   Cancellation of Contracts Cancellation is another remedy for non-performance. Cancellation brings an already existing contract to an end....