Sunday, March 7, 2021

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና እነ አቶ ቀኖ በቀለ ሰ/መ/ቁ 46816 ብድር-ወለድ-እንደተከፈለ የሚቆጠር ክፍያ

 

የሰበር መ/ቁ 46816

የካቲት 26 ቀን 2002 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- 1. ተገኔ ጌታነህ

        2. መንበረፀሃይ ታደሰ

        3. ሂሩት መለሰ

        4. አልማው ወሌ

        5. ዓሊ መሐመድ

 

አመልካች፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነ/ፈጅ እሸቱ በቀለ ቀረቡ

ተጠሪ፡- 1. አቶ ቀኖ በቀለ

        2. አቶ በቀለ ኒካ

        3. ወ/ሮ ውዴ ቀጄላ

 

ፍ ር ድ

      1ኛ ተጠሪ ከአመልካች ላይ ብር 100,000 ሲበደሩ 2ኛና 3ኛ ተጠሪዎች የአንድነትና የነጠላ የዋስትና ግዴታ የገቡ ሲሆን 1ኛ ተጠሪ ብድሩን ከፍለው ባለማጠናቀቃቸው ቀሪውን ዋና ገንዘብ እስከ 21/6/98 ድረስ ከሚታሰብ ወለድና ከሌሎች ወጪዎች ጋር እንዲከፍሉ ሰኔ 26 ቀን 1998 ዓ.ም በአመልካች ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡ 1ኛና 3ኛ ተጠሪዎች ተጠርተው ባለመቅረባቸው ጉዳዩ በሌሉበት እንዲታይ ሲደረግ 2ኛ ተጠሪ ግን ዋስ መሆናቸውን አምነው ጊዜ ተሰጥቷቸው እዳውን እንዲከፍሉና ወለድ ግን ሊከፍሉ የማይገባ መሆኑን በመግለፅ መልስ ሰጥተዋል፡፡ ክሱ የቀረበለት የምዕ/ወለጋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት 1ኛ ተጠሪ ብድር መውሰዳቸውንና ቀሪዎቹ ተጠሪዎች ዋስ መሆናቸውን ካረጋገጠ በኋላ አመልካች ለኢንሹራንስ የከፈለ ስለመሆኑ ያቀረበው ማስረጃ ስለሌለ ብር 3,267.98 እንዲከፈለው ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት የለውም፣ በፍ/ህ/ቁ 2024(ረ) መሰረት ወለዱ በሁለት አመት ውስጥ ስላልተጠየቀ እንደተከፈለ ይቆጠራል በማለት የወለድ ጥያቄውንም ውድቅ በማድረግ ተጠሪዎች ከዋናው ገንዘብ ላይ ያልተከፈለው ብር 500.00 (አምስት መቶ) ብቻ በአንድነትና በነጠላ ሊከፍሉ ይገባል በማለት ወስኗል፡፡ አመልካች በውሳኔው ቅር በመሰኘት ለኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ አመልካች በዚህ ችሎት ባቀረበው ቅሬታም የስር ፍ/ቤቶች የፍ/ህ/ቁ 2024(ረ)ን መሰረት በማድረግ ክሱን ውድቅ ማድረጋቸው መሰረታዊ የህግ ስህተት ነው በማለት ውሳኔው እንዲሻር ጠይቋል፡፡ 1ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች ተጠርተው ስላልቀረቡ ጉዳያቸው በሌሉበት እንዲታይ ታዟል፡፡ 2ኛ ተጠሪ ግን መልሳቸውን አቅርበዋል፡፡ ችሎቱም አመልካች ላበደረው ገንዘብ የሚታሰበው ወለድ በፍ/ህ/ቁ 2024(ረ) መሰረት ተቀባይነት ማጣቱ ተገቢ መሆን አለመሆኑን ለመመርመር አግባብነት ካላቸው የህግ ድንጋጌዎችና የሰበር ችሎት ከሰጠው አስገዳጅ የህግ ትርጉም ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን ተመልክቷል፡፡

      ከመዝገቡ 1ኛ ተጠሪ ከአመልካች ብር 100,000.00 ሲበደሩ 2ኛና 3ኛ ተጠሪዎች የአንድነትና የነጠላ ዋስ የነበሩ መሆኑንና ተጠሪ የተበደሩትን ገንዘብ ከፍለው ያልጨረሱ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ 1ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች ክሱን አልተከላከሉም፡፡ 2ኛ ተጠሪም ቢሆኑ ዋስ መሆናቸውን ሳይክዱ ቀሪውን ገንዘብ ጊዜ ተሰጥቷቸው ለመክፈል ጠይቀዋል፡፡ በእርግጥ ወለዱን ለመክፈል አልገደድም በማለት ክርክር ማቅረባቸው ከመዝገቡ መረዳት ተችሏል፡፡ በፍ/ህ/ቁ 2024(ረ) መሰረት በብድር የተሰጠ የገንዘብ ወለድ መጠየቅ ከሚገባበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ሁለት አመት ድረስ ሳይከፈል ከቀረ እንደተከፈለ ይቆጠራል፡፡ ይህ ድንጋጌ ባንኮች በብድር ለሰጡት የገንዘብ ወለድም ተፈፃሚነት ያለው ነው፡፡ በዚህ ድንጋጌ የተቀመጠው የህግ ግምት በፍ/ህ/ቁ 2025 ስር በተቀመጡት ሁለት አይነት የማስረጃ አይነቶች ቀሪ ሊሆን እንደሚችልና በፍ/ህ/ቁ 2026 እንደተመለከተው በመሃላ ቃል ብቻ ሊስተባበል እንደሚችል ከድንጋጌዎቹ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በመሆኑም የህሊና ግምቱ በጣም ውሱን በሆኑ ማስረጃዎች ቀሪ የሚሆንና የሚስተባበል ነው፡፡ ባንኮችን የሰጡትን ብድር በተመለከተ ግን ሁኔታው የተለየ ነው፡፡ በፍ/ህ/ቁ 2473(2) ስር እንደተመለከተው ባንኮችና ሌሎች አበዳሪ ተቋማት ደንበኞቻቸው ገንዘብ የተበደሩና የተበደሩትን ገንዘብ ያልከፈሉ መሆኑን ለማስረዳት በተመሳሳይ ሁኔታ የባንክ ተበዳሪ ብድር ያልወሰደ ወይም የወሰደውን ብድር የከፈለ መሆኑን ለማስረዳት በሰው ምስክርና በህሊና ግምት ለማስረዳት እንደሚቻል ተገልጿል፡፡ በተለይ ይህ ድንጋጌ ከፍ/ህ/ቁ 2472 ጋር ተገናዝቦ ሲታይ ባንኮችም ሆኑ ደንበኞቻቸው የሰነድ፣ የሰው ማስረጃና ሌሎች አግባብነት ያላቸውን ማስረጃዎች ማቅረብ እንደሚችሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በመሆኑም የፍ/ህ/ቁ 2026(1) ለባንኮችና ደንበኞቻቸው ልዩ ጥበቃ የሚያደርገውን የፍ/ህ/ቁ 2473 ዋጋ በሚያሳጣ ሁኔታ ሊተረጎም ስለማይገባ የፍ/ህ/ቁ 2026(1) ባንኮችንና ደንበኞቻቸውን በተመለከተ ተፈፃሚነት ሊኖረው አይገባም፡፡ በመሆኑም ምንም እንኳን ባንኮች በፍ/ህ/ቁ 2024(ረ) የሚገዙ ቢሆንም ባንኮች ያበደሩት ገንዘብ ወለድ ያልተከፈላቸው ለመሆኑ የሰው፣ የሰነድና ሌሎች ማስረጃዎች በማቅረብ ለማስረዳት ይችላሉ፡፡ ከፍ ሲል የተጠቀሱትን ድንጋጌዎች አፈፃፀም በተመለከተ ይህ የሰበር ችሎት በመ/ቁ 29181 ሰፊ ትንተና በመስጠት አስገዳጅ የሆነ የህግ ትርጉም ሰጥቶበታል፡፡

      በተያዘው ጉዳይ ተበዳሪ የሆኑት 1ኛ ተጠሪ ቀርበው ወለዱ ስለመክፈላቸው ያቀረቡት ክርክር የለም፡፡ ምንም እንኳን የፍ/ህ/ቁ 2024(ረ) ስር የተመለከተውን የህግ ግምት ፍ/ቤቱ በራሱ አነሳሽነት ማንሳት ቢችልም አመልካች ለተጠሪው ላበደረው ገንዘብ ወለዱ ያልተከፈለው ስለመሆኑ የሰው ምስክር፣ የሰነድ ወይም ሌላ ማስረጃ በማቅረብ ለማስረዳት ይችላል፡፡ በመሆኑም የስር ፍ/ቤቶች አመልካች የብድሩ ገንዘብ ወለድ አለመከፈሉን ለማስረዳት እድል ሳይሰጡትና ማስረጃዎቹን ሳይመረምሩ የፍ/ህ/ቁ 2024(ረ)ን በመጥቀስ ብቻ ወለዱ እንደተከፈለ ይቆጠራል በማለት ተጠሪዎች ከወለድ ክፍያ ግዴታቸው ነፃ በማድረግ የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት መሆኑን ተረድተናል፡፡

      በሌላ በኩል የስር ፍ/ቤቶች ባንኩ ለኢንሹራንስ የከፈለ ስለመሆኑ ያቀረበው ማስረጃ የለም በማለት ጥያቄውን ውድቅ አድርገዋል፡፡ አመልካች ለኢንሹራንስ ከፍያለሁ ካለ ስለመክፈሉ ማስረጃ ሊያቀርብ ይገባ ነበር፡፡ ማስረጃ ባለማቅረቡም ጥያቄው ውድቅ መደረጉ የህግ ስህተት ነው ሊባል አይችልም፡፡ በአጠቃላይ ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች ችሎቱ ተከታዩን ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

 

 

 

ው ሣ ኔ

1.   የምዕ/ወለጋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ 08067 ታህሳስ 28 ቀን 2001 ዓ.ም በሰጠው ውሳኔ እና የኦሮሚያ ክልል በመ/ቁ 78122 ሚያዚያ 1 ቀን 2001 ዓ.ም በሰጠው ትዕዛዝ ተሻሽሏል፡፡

2.   አመልካች ለሰጠው ብድር ወለድ ያልተከፈለው ለመሆኑ ያሉትን ማስረጃዎች መርምሮ ተገቢውን ውሳኔ እንዲሰጥ ጉዳዩን ለምዕ/ወለጋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 343(1) መሰረት መልሰናል፡፡

3.   አመልካች ለዳኝነት ያወጣውን ገንዘብ በደረሰኙ መሰረት ተጠሪዎች በአንድነትና በነጠላ ይክፈሉ፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፡፡ ለመዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

ራ/ታ

No comments:

Post a Comment

Cancellation of Contracts

   Cancellation of Contracts Cancellation is another remedy for non-performance. Cancellation brings an already existing contract to an end....