Sunday, March 7, 2021

አቶ ጥበቡ እምሩ እኛ አቶ ሙሉጌታ ካሴ ሰ/መ/ቁ 47987 በባለመሬቱ ፈቃድ ሕንፃ የገነባ ወይም ዛፍ የተከለ ሰው የሚኖረው መብት

 

የሰ/መ/ቁ 47987

የካቲት 9 ቀን 2002 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ

        ሐጐስ ወልዱ

        ሂሩት መለሰ

        ብርሃኑ አመነው

        አልማው ወሌ

 

አመልካች፡- አቶ ጥበቡ እምሩ - ቀረቡ

ተጠሪ፡- አቶ ሙሉጌታ ካሴ - ቀረቡ

 

      መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

ፍ ር ድ

      በዚህ መዝገብ የቀረበው ጉዳይ የይዞታ ክርክር የሚመለከት ነው፡፡ አመልካች ሥር ፍ/ቤት ተጠሪ ላይ ያቀረበው ክስ ይዞታዬን ያለአግባብ በእጁ አድርጐ ቤት ሰርቶበታል እና እንዲያስረክበኝ ይወሰንልኝ የሚል ሲሆን ተጠሪ በበኩሉ መሬቱን በንጥጥፍ በስምምነት በእጅ ያደረገ መሆኑን ተከራከረ፡፡ የሥር ፍ/ቤትም በግራቀኙ መካከል የመሬት ልውውጥ ስምምነት መኖሩን አረጋግጧል፡፡ ነገር ግን የልውውጥ ስምምነት በክልሉ ደንብ ቁጥር 51/99 መሠረት በወረዳው አስተዳደር ክፍል አልተመዘገበም በሚል ሕጋዊ ውጤት ሊኖረው እንደማይገባ ወስኖ ግራቀኙ ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ አመልካች ተጠሪ ላወጣው ወጪ በፍ/ብ/ህ/ቁ 1179/1/ እና 1180 መሠረት የሕንፃውን (የቤቱን) ዋጋ ከፍሎ እንዲረከብ ፈርዷል፡፡

      ይህ ፍርድ በክልሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት እና ሰበር ሰሚ ችሎት ፀንቷል፡፡

      አመልካች ነሐሴ 4/2002 ዓ.ም ጽፎ ያቀረበው አቤቱታ ተጠሪ በነፃ የኖረበትን ይዞታ የቤት ግምት ክፈል መባሉ ተገቢ አይደለም ይሻርልኝ የሚል ነው፡፡

      ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩ ከፍ/ብ/ህግ ቁ.1176 እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎች አንፃር ለመመርመር ተጠሪን አስቀርቧል፡፡ ተጠሪ በጽሑፍ ያቀረበው መልስ የጉዳዩን አመጣጥ በዝርዝር በመግለፅ በሥር ፍ/ቤት ውሳኔ ቅር ተሰኝቶ ለክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት በቀጠሮ ላይ መሆኑን ጠቅሶ በዋናነት ግን የመሬት ልውውጥ ስምምነት ሥልጣን ባለው አካል ቀርቦ የተመዘገበ መሆኑን በመጥቀስ ውል በሕግ ፊት የፀና ነው ይባልልኝ ሲል የተጨማሪ ማስረጃ ጥያቄም አቅርቧል፡፡

      እኛም የቀረበውን ጉዳይ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር ከሕጉ ጋር አገናዝበን መርምረናል፡፡

      በመሠረቱ ተጠሪ የአመለካችን መሬት የያዘው እና ቤት የሰራበት በልውውጥ ስምምነት መነሻ መሆኑን የሥር ፍ/ቤት አረጋግጧል፡፡ ስምምነቱ በሚመለከተው አካል ዘንድ ስለመመዝገቡ ተጠሪ ሥር ፍ/ቤት ዘንድ ያቀረበው ማስረጃ ስለመኖሩ መዝገቡ አይስረዳም፡፡ ተጠሪ ማስረጃ አለኝ የሚል ከሆነም በራሱ በኩል በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕጉ በተደነገገው አግባብ ደረጃውን ጠብቆ በደረጃው ባሉት ፍ/ቤቶች ተገቢውን ዳኝነት ከሚጠይቅ በቀር ተጠሪ በሆነበት መዝገብ ተጨማሪ ማስረጃ መጠየቁ አግባብነት የለውም፡፡ ከዚህም አልፎ የሰበር ሰሚ ችሎት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 345 አዲስ ማስረጃ ሊሰማ የሚችልበት ጉዳይ አይደለም፡፡ በአመልካች በኩል ከቀረበው አቤቱታ እና በዚህ ችሎት ከተያዘው ጭብጥ አንፃር ጉዳዩ ሲመረመር አመልካች በስምምነት ለተጠሪ መሬቱን የሰጠ መሆኑ ከፍ ሲል ተመልክተናል፡፡ ተጠሪም በበኩሉ በአመልካች ይዞታ ላይ ቤት መሥራቱ እና ዛፍ(ችግኝ) እና አትክልት ማልማቱ ከአመልካች ጋር በተደረገ ስምምነት መነሻ መሆኑን የሥር መዝገብ ያስረዳል፡፡ እንግዲህ በባለመሬቱ ፈቃድ ሕንፃ የገነባ ወይም ዛፍ የተከለ ሰው የሚኖረው መብት አስመልክቶ የፍ/ብ/ሕግ ድንጋጌ ቁ.1176 እና 1179 ድንጋጌ እንደሚያስረዳው ይህ ሰው የዚሁ ሀብት ባለመብት መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ባለመብት ነው ከተባለ በኋላ ባለመሬቱ ማስለቀቅ ሲፈልግ የሚኖረው የግራ ቀኙ መብት እና ግዴታም በተከታዮቹ ድንጋጌዎች ተዘርዝረዋል፡፡

      ከእነዚህ የመጀመሪያው በሁለቱ መካከል በሚደርስ ስምምነት መፈጸም ስምምነት ካልተደረሰ ሕጉ ባስቀመጠው አማራጭ ማስፈጸም ነው፡፡

      ከእነዚህ መርሆዎች አንፃር በተያዘው ጉዳይ የሥር ፍ/ቤት የፍ/ብ/ሕ/ቁ.1179/1/ እና 1180 መሠረት በማድረግ አመልካች ሳይቃወም ይልቁንም በልውውጥ ስምምነት መሠረት ተጠሪ በአመልካች ይዞታ ላይ ለሰራው ቤት እና ላለማው አትክልት ተገቢውን ካሣ ከፍሎ ማስለቀቅ ይገባል ሲል የሰጠው ፍርድ በሕግ ረገድ መሠረታዊ የሕግ ስሕተት አለው የሚያሰኝ ሆኖ አላገኘነውም፡፡

      ስለሆነም አመልካች በይዞታዬ ላይ ተጠሪ ለሰራው ቤት ግምት ካሣ መክፈል የለብኝም ሲል ያቀረበው አቤቱታ የሕግ መሠረት የለውም ብለናል፡፡

ው ሳ ኔ

  1. የሠከለ ወረዳ ፍ/ቤት በመ/ቁ 02368 የሰጠው ፍርድ የምዕራብ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ 32047 የሰጠው ትዕዛዝ እና የአማራ ብ/ክ/ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁ 01818 የሰጠው ትዕዛዝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁ.348(1) መሠረት ፀንቷል፡፡

ግራ ቀኝ የዚህን ፍ/ቤት ወጪና ኪሣራ ይቻቻሉ፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

ራ/ታ

No comments:

Post a Comment

Cancellation of Contracts

   Cancellation of Contracts Cancellation is another remedy for non-performance. Cancellation brings an already existing contract to an end....