Tuesday, March 9, 2021

አቢሲኒያ ባንክ እና ዘውዱ ነጋ ሰ/መ/ቁ 51001 የመያዣ ውል- የአደራ ውል

 

የሰበር መ/ቁ 51001

ጥር 26 ቀን 2002 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- 1. ተገኔ ጌታነህ

         2. መንበረፀሐይ ታደሰ

         3. ሐጐስ ወልዱ

         4. ሂሩት መለሠ

         5. አልማው ወሌ

 

አመልካች፡- አቢሲኒያ ባንክ - መርአዊ ታደሰ ቀረቡ

ተጠሪ፡- ዘውዱ ነጋ - ከጠበቃው ደሳለኝ አለሙ ክብረት ጋር ቀረቡ

       መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

ፍ ር ድ

       በዚህ መዝገብ አከራካሪ ሆኖ የቀረበው ነጥብ ተጠሪ ንብረቴ ነው በማለት ክስ የመሠረቱበት ሰሊጥ አመልካች ከሌላ ሰው ጋር ባደረገው ስምምነት በመያዣ የያዘው የመያዣ ሠጪው ንብረት ነው ወይንስ የተጠሪው ንብረት የሚለው ነው፡፡ ክርክሩ ከፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ሲጀመር ከሣሽ የነበረው ተጠሪ ሲሆን፣ ተከሳሽ ደግሞ ፐርፍ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ የሚባል ኩባንያ ነው፡፡ ተጠሪ ክስ ሊመሰርት የቻለው በአደራ ያስቀመጥኩትን 2257.064 ኩንታል ነጭ የሁመራ ሰልጥ ያልመለሰልኝ በመሆኑ በፍርድ ኃይል ተገዶ ይመልስልኝ በማለት ነው፡፡ ክሱን በመከተልም ሰሊጡ እንዲታገድ ጥያቄ በመቅረቡ ፍ/ቤቱ ሰሊጡ በሚገኝበት በናይል ቡና ላኪ ኃ/የተወሰነ የግል ማህበር መጋዘን እንዳለ ተከብሮ እንዲቆይ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ክርክሩ ከመወሰኑ በፊት ከሣሽና ተከሣሽ ጉዳዩን በእርቅ ጨርሰው ስለመጡ ይህንኑ ለፍ/ቤቱ አቅርበው በስምምነቱ መሠረት እንዲፈፀም ትዕዛዝ አሰጥተዋል፡፡ ቀደም ሲል ተሰጥቶ የነበረው የእግድ ትዕዛዝም ፍ/ቤቱ አንስቶአል፡፡ አመልካች ክርክሩ ውስጥ የገባው ከዚህ በኋላ ነው፡፡

       ከመዝገቡ እንዳየነው አመልካች መቃወሚያ ያቀረበው በፍብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁ.358 የተመለከተውን ድንጋጌ መሠረት በማድረግ ሲሆን፣ ዳኝነት የጠየቀውም ከሣሽ እና ተከሳሽ ያደረጉት የእርቅ ስምምነት በመያዣ የያዝኩትን ሰሊጥ የሚመለከት በመሆኑ ይጐዳኛል፤ ይሰረዝልኝ በማለት ነው፡፡ ፍ/ቤቱ የሁለንም ወገኖች ሃሣብ ከተቀበለ በኋላ፣ የአመልካችን መቃወሚያ ውድቅ በማድረግ ውሣኔ ሰጥቶአል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አመልካች ውሣኔውን በመቃወም ለፌዴራል ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ በማቅረቡ ክርክሩ በአመልካች እና በተጠሪ መካከል ተካሂዶአል፡፡ በመጨረሻም ፍ/ቤቱ የአመልካችና ክርክር ውድቅ በማድረግ ለክርክሩ መነሻ የሆነው ሰሊጥ አመልካች ለሥር ተከሳሽ ለሰጠው ብድር በመያዣነት የያዘው አይደለም፡፡ ሰሊጡ የሥር ተከሳሽ በአደራ ያስቀመጠው የተጠሪ ንብረት በመሆኑ በተጠሪ እና በሥር ተከሳሽ መካከል ታሕሣሥ 14 ቀን 2001 ዓ.ም የተደረገው የእርቅ ስምምነት የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ማፅደቁ ተገቢ ነው፡፡ በመሆኑም በእርቅ ስምምነቱ መሠት ይፈጸም በማለት ወስኖአል፡፡ የሰበር አበቱታው የቀረበው በዚህ ላይ ነው፡፡

       በበኩላችንም አመልካች ታህሣሥ 8 ቀን 2002 ዓ.ም በጻፈው ማመልከቻ ያቀረበውን አቤቱታ መሠረት በማድረግ ተጠሪን አስቀርበን ክርክሩን ሰምተናል፡፡ በመቀጠልም አከራካሪ የሆነውን ጭብጥ ከግራ ቀኝ ወገኖች ክርክር፣ አቤቱታ ከቀረበበት ውሳኔ እና ከሕጉ ጋር አገናዝበን መርምረናል፡፡

       ከሠር ጀምሮ ከተደረገው ክርክር መገንዘብ እንደቻልነው በተጠሪ እና በሥር ተከሳሽ መካከል የተፈጠረው ግንኙነት የተመሠረተው ግንቦት 17 ቀን 2000 ዓ.ም በተፈፀሙት የአደራ ውል ነው፡፡ የአደራ ውሉ ከመፈረሙ በፊት ማለትም ከግንቦት 13 እስከ 18 ቀን 2000 ዓ.ም ድረስ በነበሩት ቀናት ውስጥ ሰሊጡ ወደ መጋዘኑ ስለ መግባቱም በፌዴራል ጠ/ፍ/ቤት በተደረገው ክርክር በማስረጃ የተረጋገጠ ለመሆኑ በውሳኔ ላይ ተመልክቶአል፡፡ ተጠሪ በአደራ አስቀማጩ ላይ ክስ የመሠረተው ሰሊጡን ሊመልስልኝ አልቻለም በማለት ሲሆን፣ አመልካች ደግሞ ሰሊጡ በመያዣ የያዝኩት ነው፡፡ ለተጠሪ ሊሰጥ አይገባም የሚል መከራከሪያ ይዞ ነው ወደ ክርክሩ የገባው፡፡ የመያዣ ውሉ ተደረገ የተባለው በአመልካች እና በሥር ተከሳሽ (ሰሊጡን በአደራ አስቀምጦአል ተብሎ በተከሰሰው) መካከል እንደሆነም አላከራከረም፡፡ በመሆኑም ለክርክሩ መነሻ በሆነው ሰሊጥ ላይ አመልካች መብት አለው ወይስ የለውም የሚለውን ነጥብ ከማየት በፊት ከመሠረቱ ሰሊጡ የማን ንብረት ነው? የሚለውን ጥያቄ መመለሱ አግባብ ይሆናል፡፡

       የአመልካች ክርክር በዋነኛነት የተመሠረተው የሥር ተከሳሽ በናይል ቡና ላኪ ኃ/የተ/የግል ማህበር መጋዘን በተለያዩ ጊዜያት የሚያስገባው ሰሊጥ በመያዣነት ለሚያዝ ህዳር 13 ቀን 98 ዓ.ም በተደረገው የሶስትዮሽ ውል አለኝ በሚለው ላይ ነው፡፡ ለክርክሩ መነሻ የሆነው መጠኑ በትክክል የተገለጸው ሰሊጥ በእርግጥ እና በተለየ ሁኔታ በመያዣ ለመያዙ የሚያስረዳለት ሌላ ማስረጃ ግን አላቀረበም፡፡ ሰሊጡ የማነው? በሚለው ነጥብ ላይ በዝርዝር ክርክር የተደረገው በፌዴራል ጠ/ፍ/ቤት ሲሆን፣ በዚህ ሂደትም ፍ/ቤቱ ሰሊጡ በተጠሪ ስም ከጎንደር ተጭኖ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣ በቀጥታ ለሥር ተከሳሽም ተቀብሎ በናይል ቡና ላኪ ኃ/የተ/የግል ማህበር መጋዘን ውስጥ በማስቀመጡና፣ ለዚህም ግንቦት 8 ቀን 2000 ዓ.ም የተጻፈ ቁጥር 0119 እና 0001 የሆኑ፣ ግንቦት 9 ቀን 2000 ዓ.ም የተጻፈ ቁጥሩ 0116 የሆነ፣ ግንቦት 11 ቀን 2000 ዓ.ም የተጻፈ ቁጥሩ 0117 የሆነ፣ ግንቦት 13 ቀን 2000 ዓ.ም የተጻፈ ቁጥሩ 0118 እና 0119 የሆኑ እና ግንቦት 14 ቀን 2000 ዓ.ም የተጻፈ ቁጥር 0120 የሆነ የማስጫኛ ሰነዶች በአስረጂነት መቅረባቸውን አረጋግጠዋል፡፡ የማስጫኛ ሰነዶች የመኪናው ታርጋ /ሠሌዳ/ ቁጥር የሹፌሩ ስም እና ስልክ ቁጥር፣ የጭነቱ ልክ፣ ወዘተ በዝርዝር የያዙ እንደሆኑም ጠ/ፍ/ቤቱ አረጋግጦአል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ተጠሪ ሰሊጡን ወደ አዲስ አበባ ያመጣው ለመሸጥ እንደሆነ፣ ነገር ግን በጊዜው የገበያ ዋጋ ስለዋዠቀበት የተሻለ ገበያ እስኪያገኝ ድረስ በአደራ እንድቀመጥለት ማድረጉን ፍ/ቤቱ ማጣራቱን በውሳኔው ላይ ተገልጿል፡፡ ፍ/ቤቱ እነዚህን ማስረጃዎች ከመረመረ እና ከግራ ቀኝ ወገኖች ክርክር አገናዝቦ ከመዘነ በኋላም ለክርክሩ መነሻ የሆነው ሰሊጥ የተጠሪ ንብረት ነው ወደሚለው መደምደሚያ ደርሶአል፡፡

       እንደምንመለከተው ለክርክሩ መነሻ የሆነው ሰሊጡ የተጠሪ ንብረት ስለመሆኑ በሕግና በፍሬ ነገር ረገድ የቀረበውን ክርክር የመመርመር ስልጣን ባለው ጠ/ፍ/ቤት ተረጋግጦአል፡፡ አመልካች የመያዣ ውል ያደረገው ከተጠሪ ጋር አይደለም፡፡ የመያዣ ውል አደረግሁ የሚለው ከሥር ተከሣሽ ፐርፍ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ጋር ሆኖ መሠረቱም በየጊዜው ተሰጡ የተባሉት ብድሮች እንደሆኑ በክርክሩ ገልጾታል፡፡ በሰሊጡ ላይ መብት አለኝ የሚለው የመያዣ ውሉን መሠረት በማድረግ እስከሆነም ድረስ ሰሊጡ የመያዣ ሰጪው ንብረት መሆኑን ሊያስረዳ ይገባል፡፡ እንደምናየው ግን የመያዣ ውል ማድረጉን ከማሳየት አልፎ ለክርክሩ መነሻ የሆነው ሰሊጥ የመያዣ ሰጭው ንብረት መሆኑን ሊያስረዳ እንዳልቻለ ጠ/ፍ/ቤቱ አረጋግጦአል፡፡ በመሆኑም ለክርክሩ እልባት ለመስጠት መታየት ያለበት ሰሊጡ የማን ንብረት ነው ለሚለው ጥያቄ የተገኘው ምላሽ እንጂ አመልካች ከሥር ተከሳሽ ጋር የመያዣ ውል አድርጎአል ወይስ አላደረገም የሚለው አይደለም፡፡ በመጨረሻም በማስረጃ ተረጋግጦ በተደረሰው የፍሬ ነገር ድምዳሜ ላይ የቀረበው የሰበር አቤቱታ በሕግ አተረጓጎም ረገድ የተፈጸመ መሠረታዊ የሕግ ስህተት መኖሩን የሚያሳይ ባለመሆኑ የሰበር ችሎቱ የሚያርመው አይሆንም (የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 80/3//ሀ/ እና የፌዴራል ፍ/ቤቶች አዋጅ ቁ.25/88 አንቀጽ 10 ይመለከተዋል)

ው ሣ ኔ

  1. የፌዴራል ጠ/ፍ/ቤት በፍ/ብ/ይ/መ/ቁ 46144 ታህሳስ 1 ቀን 2002 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁ.348(1) መሠረት ፀንቶአል፡፡
  2. አመልካች ያቀረበው የሰበር አቤቱታ ተቀባይነት የለውም ብለናል፡፡
  3. በዚህ ሰበር ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ በተመለከተ ግራ ቀኝ ወገኖች ይቻቻሉ፡፡ መዝገቡ ይመለስ፡፡

 

ት ዕ ዛዝ

 

       ታሕሣሥ 4 ቀን 2002 ዓ.ም ተሰጥቶ የነበረው የእግድ ትዕዛዝ ተነስቶአል፡፡ ለሚመለከተው ይጻፍ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

 

ራ/ታ

No comments:

Post a Comment

Cancellation of Contracts

   Cancellation of Contracts Cancellation is another remedy for non-performance. Cancellation brings an already existing contract to an end....