Sunday, March 7, 2021

የውል ህግ ተግባራት

(ምንጭ፡ የተሻሻለው የውል ህግ ሞጁል (ለሥራ ላይ ሠልጣኞች የተዘጋጀ)

የተዋዋዮችን ግንኙነት ማደራጀት (the coordination role)

ውል ማለት ንብረታቸውን የሚመለከቱ ተነፃፃሪ ግዴታዎችን ለማቋቋም ለመለወጥ ወይም ለማስቀረት ሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ ሰዎች መካከል የሚደረግ ስምምነት ነው የፍ.ብ.ህ.ቁ 1675 (1) ፡፡ ስምምነቱ የሚቆመው በነፃ ፈቃድ ላይ ነው፡፡ ይህ በሁሉም የህግ ስርዓቶች ያለ መሰረታዊ ሀሳብ ነው፡፡ በነፃ ፈቃድ የመሠረቱት ውል ሊከበርን ይገባል ብለው ባሰቡት መንገድ የሚፈልጉትን ቁምነገር እንዲያካትት አድርገው ይቀርጹታል፡፡ ይህም በተዋዋዮች መካከል ዕርካታን ያመጣል ተብሎ ይታሰባል፡፡

ይሁንና የሰው ልጅ ውሱንነት (Limited rationality) ያለበት በመሆኑ የህይወት አጋጣሚዎች በስምምነታቸው ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉትን ተፅዕኖ አስቀድሞ ለማየት ከመቸገር ክፍተቶቸ ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ውሉ ምሉዕነት ይጎድለዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ማን ምን ማድረግ አለበት የሚለው ጉዳይ በተዋዋዮች መካከል ውዝግብ ሊፈጥር ይችላል፡፡ በመተማመን ላይ የሚመሠረቱ ግንኙነቶችን ይጎዳል፡፡ ዳፋውም ተከታታይ የሆኑ የንግድ ትስስሮችን ያበላሻል፡፡ የልውውጥ ሂደትን ይጎዳል ማለት ነው፡፡ የውል ህግ መኖር አስፈላጊነት የሚመጣው እዚህ ላይ ነው፡፡ ተዋዋዮች ሳይገልጿቸው ያለፏቸው ነገር ግን ግንኙነታቸውን የሚጎዱ ነገሮች ሲኖሩ ህጉ በነርሱ ዝምታ ውስጥ የታለፈውን ጉዳይ ለመሸፈን ይመጣል “Default rules” ይባላሉ፡፡ ከተዋዋዮቹ ውስጥ ማን ምን እንደሚጠበቅበት በመግለጽ እያንዳንዳቸው በውሉ ውስጥ የሚኖራቸውን ሚና ያጠራል፣ ነገሩ እንዴት መፈጸም እንዳለበት በዝርዝር በማስፈር አንዱ ወገን በውሉ ዝምታ ምክንያት ተገቢ ያልሆነ ጥቅም እንዳያገኝ ይገታል፡፡ በተዋዋዮች መካከል የሚኖረውን ትርምስ ያስቀራል፡፡ ወንድማማችነት ይፈጠራል፡፡ ግንኙነታቸውንም መልክ በማስያዝ ልውውጦችን ቀና ያደርጋል፡፡ በሌላ አገላላጽ ለጋራ ጥቅም ኃላፊነትን በመደልደል በተዋዋዮች መካከል ሊኖር የሚገባውን ግንኙነት ያደራጃል (ያቀናጃል) ማለት ነው፡፡ ደግምም “Default rules”ን በመተማመን በያንዳንዱ የግንኙነቶቻቸው ሂደት ውስጥ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እየተጨነቁ ሳያስቡ ግንኙነቶቻቸውን እንዲመሩ ይረዳል፡፡

አፈፃፃማቸው ጊዜ የሚጠይቅ ስምምነቶችን አስተማማኝ ማድረግ 

ውሎች በአብዛኛው የሚፈፀሙት እጅ በእጅ (on the spot) በሚደረግ ልውውጥ ሲሆን የትኛውም ወገን ከስምምነቱ አገኛለሁ የሚለውን ጥቅም ስምምነቱ እንደተፈፀመ ያገኛል፡፡ ውሉ የሚመሰረተውም የሚፈፀመውም እዚያው ላይ በመሆኑ በለውጡ የሚያገኘው የሚፈልገውን እንደሆነ ይታሰባል፡፡ በየዕለቱ የሚታዩትን ልውውጦች ያህል ውዝግብ አለመኖሩ የሚያሳየውም ይህንኑ ነው፡፡

ይሁንና በገሃዱ ዓለም ስምምነቶች ሁሉ እጅ በእጅ የሚከናወኑ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ አፈፃፃማቸው በጊዜ ሂደት የሚከናወን ስምምነቶችም አሉ፡፡ በውሉ አመሰራረትና በአፈጻጸሙ መሃል የጊዜ ክፍተት ሲኖር ተዋዋዮች እንደስምምነቱ ቃላቸውን የሚያከብሩ ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን ያስቸግራል፡፡ መተማመን ይጎድለናል፡፡ እናም እንዲህ ያሉ ስምምነቶች ውስጥ ለመግባት እናመነታለን፡፡ ብንገባም እንኳ ሊደርስ የሚችለውን ኪሳራ በማሰብ ስምምነቶቻችንን ከምናውቃቸው እና ከምንተማመንባቸው ሰዎች ጋር ብቻ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ የልውውጡ አድማስ ይጠባል ማለት ነው፡፡ ይህ የሸቀጦችን ዋጋ ያንራል፤ በመደበኛ ሂደት የሚኖረውን የልውውጥ ወጪ ከፍ ያደርጋል፡፡ የውል ህግ መኖር ይህ እንዳይሆን ይጠብቃል፡፡ ሰው በቃሉ ይታሰራል (pacta sur servanda) [የፍ.ብ.ህ.ቁ 1731(1)] የሚለው ጽንሰ ሃሳብ መሠረትም በፈቃድ የገቡትን ግዴታ ተዋዋዮች እንዲያከብሩ በማድረግ የሞራል ግዴታ ይጥልባቸዋል፡፡ አንዱ ተዋዋይ በሌላው ላይ ያደረሰውን ጉዳት እንዲክስ [የፍ.ብ.ህ.ቁ. 1790 እና 1791[ በመደንገግም ጉዳት ሊደርስበት የሚችል ተዋዋይ ቢኖር እንዳይሰጋ ያደርጋል፡፡ ጥበቃው በውሎች ላይ ሊኖር የሚችለውን መተማመን ይጨምራል፤ ይህ ባይሆን ኖሮ ማንም ሰው ያለውን ለሌላው አሳልፎ ይሰጣል ብሎ ማሰብ ይከብዳል፡፡

አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ጥቅሞቻችን በሁኔታዎች ላይ የተመሰረቱ ይሆኑና ልናገኝ የምንፈልገው ነገር ከአንድ ክስተት በፊት ወይ በኃላ የመምጣቱ ነገር ውል ለማድረግ በሚኖረን ውሳኔ ላይ የራሱ የሆነ ተጽዕኖ ይኖረዋል፡፡ በምሳሌ ለመግለጽ ያህል አንድ አደጋ ከተከሰተ በኃላ ንብረቱ የወደመበት ሰው አረቦን (premium) ልክፈልህ እና በንብረቴ ላይ የደረውን ጉዳት ጠግንልኝ በማለት አንድን የኢንሹራንስ ኩባንያ ቢጠይቅ ኩባንያው ፈቃደኛ አይሆንም፤ በተመሳሳይ ሁኔታም ጉዳት ከመድረሱ በፊት የንብረቱ ባለቤት የሆነ ሰው አረቦን (premium) የመክፈል ዝንባሌ አይኖረውም ወይም አነስተኛ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ልውውጥ በእጅ ለእጅ ገበያ ውስጥ ማግኘት አይቻልም፡፡ አስቀድሞ የሚደረጉ የቃል መግባቶችን የሚጠይቁ ናቸው:: ታዲያ ህጉ ይህን እና መሰል ስምምነቶች እንዴት መመስረትና መመራት እንዳለባቸው ሥርዓት በማበጀት ልውውጡን ቀና ያደርጋል፡፡

ስለሆነም በአንድ ውል መመስረት እና በአፈፃፀሙ መሃል ያለው የጊዜ መስፋት ስለ አፈፃፀሙ ያለንን ዕምነት ሳይሸረሽር፣ ወደፊት ሊኖረን የሚገባውን ግንኙነትም ከወዲሁ ለማዘጋጀት የሚያስችል ማዕቀፍ በማዘጋጀት ልውውጦችን ቀና እና አስተማማኝ ያደርጋል ማለት ይቻላል፡፡

 ስምምነቶች የሚኖራቸውን ጉድለት መሙላት

በህግ ክልከላ የተደረገበት ካልሆነ በቀር ውል ያቋቋሟቸው ወገኖች ስምምነታቸውን በፈቀዱት መንገድ ለመፈጸም ቃል የሚገቡበት ሰነድ ነው፡፡ በዚህ ስምምነት ተዋዋዮች ምን ሰጥተው ምን መቀበል እንደለባቸው ያውቃሉ፣ መቼ እና እንዴት ማከናወን እንዳለባቸውም በዝርዝር በመግለጽ ይስማማሉ፡፡ ሆኖም ስምምነታቸው በሚከሉት ምክንያቶች ምሉዕ ላይሆን ይችላል፡፡

             . የተዋዋዮች ውሱንነት

ተዋዋዮች በአንድ ጉዳይ ሊደራደሩ ይችላሉ፡፡ ሲስማሙ ውዝግብ ቢነሳ እንኳ ማንም ሰው ሊረዳቸው በሚችል መንገድ የተስማሙባቸውን ነጥቦች በግልጽ እና በዝርዝር ለመቅረጽ ይጥራሉ፡፡ ነገር ግን ሰዎች ውሱን አዕምሮ ያለቸው በመሆኑ በጊዜ ሂደት የህይወት ውጣ ውረድ (externalities) በግንኙነታቸው ውስጥ ሊፈጥር የሚችለውን ተፅዕኖ አስተማማኝ በሆነ መንገድ ሊያውቁ አይችሉም ወይም ለማወቅ ይቸገራሉ፡፡ ስለሆነም በግንኙነታቸው ሚዛን ላይ ጊዜ የሚፈጥረውን ተፅዕኖ አለማወቃቸው ውሉ ምሉዕነት እንዲጎድለው ምክንያት ይሆናል፡፡              

 .  ዝርዝር መሆን የሚጠይቀው ዋጋ

ሰዎች ሊኖራቸው የሚችለውን የውል ግንኙነት ምን መምሰል እንዳለበት እስከ ፍፃሜው ድረስ አስቀድሞ በማየት የተሳካላቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ዋና ከሚባሉ ጉዳዮች አልፈው የታዩዋቸውን ጥቃቅን ዝርዝሮች ሁሉ መፃፍና መስማማት ላይፈልጉ ይችላሉ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ጥቃቅን ዝርዝር ላይ የሚደረገው አለመስማማት ዋና እና መሰረታዊ ነው የተባለውን ጉዳይ ሊያደፈርስ ይችላል፡፡ በሁለተኛ ደረጃም በእያንዳንዱ ጥቃቅን ዝርዝር ላይ ለመነጋገር መጨነቅ የራሱን ጊዜ የሚወስድና ወጪንም የሚጠይቅ ሂደት በመሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም ተዋዋዮች በ “default rules” በመተማመን ዋና ነገሮች ላይ ብቻ በማተኮር ዝርዝሩን ሊተውት ይችላሉ፡፡

        . ውል በትክክል ሊፈጸም የሚችል መሆኑን ማረጋገጥ አለመቻል

በብዙ አጋጣሚዎች ስምምነቶች እንደተዋዋዮች ፈቃድ መፈጸማቸውን ማረጋገጥ ይቻል ይሆናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን እርግጠኛ ለመሆን አይቻልም:: እጅ በእጅ በሚደረግ ልውውጥ ውስጥ እንኳ ይህን መተማመን ለማግኘት ያስቸግራል:: አንድን ምርት በግዢ የተቀበለ ሰው የተረከበው ምርት ጥራት፣ አሰራር በውሉ ላይ በሰፈረው ዓይነት ስለመሆኑ በርክክቡ ጊዜ ለመረዳት ይከብደው ይሆናል፡፡ ተፈላጊው ማሽን ለተፈለገበት ዓለማ የተገባ መሆኑን ለማወቅ በዕጃችን ከገባ በኋላ ሥራ ላይ ስናውለው ችግር መፍጠሩን እስክናይ የተረከብነው በስምምነቱ መሰረት እንደሆነ ልናስብ እንችላለን ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታም የተረከብነው የስንዴ ዱቄት ጊዜው ያለፈበት የተበላሸ መሆኑን የምንረዳው በርክክቡ ጊዜ ሳይሆን ከርክክቡ በኃላ ስናቦከውም ሆነ ስንጋግረው ከደንበኛው ዱቄት የምንጠብቀውን ውጤት ያልሰጠን መሆኑን ስናይ ነው እንደውሉ ያልተፈፀመልን መሆኑን የምንረዳው፡፡

ታዲያ ውሉ በሚመሰረትበት ጊዜ እንዲህ ያሉትን ሁኔታዎች ቀድመን ለማወቅ እንቸገራለን፡፡ ምክንያቱም በዚያን ጊዜ በነገሩ ላይ ያለን ዕውቀት ዝቅተኛ መሆን ወይም በጊዜው ዝርዝር ነገሮችን ማረጋገጥ ውስብስብነት ያለው፣ ጊዜና ወጪን የሚጠይቅ መሆኑ በዝርዝሩ ላይ በርግጠኝነት ለመደራደር እንዳንችል ያደርገናል፡፡ ስለዚህም መሠረታዊ በሆኑት ላይ ብቻ በማተኮር ቀሪዎችን ዝርዝሮች እናልፋለን፡፡ አንዱ ተዋዋይ አውቆት ቢሆን እንኳ ፍርድ ቤቶች በጉዳዩ ላይ ያላቸውን የዕውቀት ውሱንነት በመገመት በዕኩይ መንፈስ ነገሩ ሳይነሳ እንዲያልፍ መፈለግም ሌላው ለዝርዝር ነገሮች መታለፍ አንድ ምክንያት ሊሆን የሚችል ነው፡፡

በአጠቃላይ ሲታይ አንድ ውል በየትኛውም ምክንያት ቢሆን ምሉዕነት ላይኖረው ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ህጉ ተዋዋዮች በውሉ ጊዜ የነበራቸውን ሀሳብ ምን እንደነበር ለማወቅ ዳኛው ጥረት ማድረግ እንዳለበት ያዛል፡፡ ይህን ለማድረግ የተዋዋዮች ግንኙነት ምን እንደነበር፣ በውሉ አፈፃፀም ሂደት የነበራቸው ሚና መለየት፣ ፍትህ እና የኢኮኖሚ ሥልጠት እንዲሁም ሌሎችንም ምክንያታዊ የሆኑት ነገሮችን የሚጠይቁትን ሁሉ ከግምት ውስጥ በማስገባት መመርመር የሚጠይቅ ይሆናል ማለት ነው፡፡ የሆኖ ሆኖ ህጉ የአተረጓጎም ሥርዓቶችን በማበጀት ክፍተቱን (የውሉን ጉድለት) ይሞላል፡፡

በህግ ትርጉም ላይ እራሱን ችሎ በተዘጋጀው የስልጠና ማቴርያል ይህ ርዕስ በዝርዝር የሚነሳ ቢሆንም እዚህ ላይም የተወሰኑ ደንቦችን ማንሳቱ ተገቢነት ይኖረዋል።

ውሎች በሚዘጋጁ ጊዜ አስፈላጊ ጥንቃቄዎች እንደሚደረጉ ይታመናል። ይሁን እንጂ በውልም በሌሎች ህጎች ውስጥ የአንድን ቃል ዓረፍተነገር ወይም ሃረግ ሁለትና ከዚያ በላይ መልእክቶችን ይዞ የሚገኝባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው። ተዋዋይ ወገኖች በዚህ ቃላቶችና ትርጉም ላይ ባለመስማማት ክርክር ያቀርባሉ። ዳኞች በእርግጥም በውሉ ውስጥ ያሉ ቃላት ወይም ዓረፍተነገር ግልፅ አለመሆኑን ካረጋገጡ ትርጉም መስጠት የግድ ይላቸዋል። የሚሰጠው ትርጉም በተዋዋይ ወገኞች መብት ላይ የሚያጋጥመውን ችግር ሁሉ በመገንዘብ ተገቢው ጥንቃቄ ሁሉ ይደረጋል።  በኢትዮጲያ የፍትሃብሄር ህግ ውሥጥ ዳኞጭ ውሎችን ሲተጉሙ ሊመሩባችው የሚገቡ መሰረታዊ የትርጉም ደንቦች ተቀምጠዋል። እነዚህ ደንቦች የሚከተሉት ናቸው።

    የመጀመሪያው ደንብ በፍታብሄር ህጉ አንቀፅ( 1732)ላይ የተመለከተው ነው ። ይህ ድንጋጌ የቅን ልቦና አተረጎገም ደንብን የያዘ ነው። በዚህ ደንብ መሰረት በተዋዋዮቹ መካከል ሊኖር የሚገባውን የቅንነትና የመተማመን ግንኙነት መሰረት በማድረግና በጉዮቹ ውስጥ ያለውን ልማዳዊ ስርአት በመከተል ውሎች በቅን ልቦና ሊተረጎሙ ይገባል። የዚህ ድንጋጌ አንኳር  ሃሳብ ውል በሚተረጎምበት ጊዜ በተቻለ መጠን ውሉ የሚፈርስበትን ሳይሆን ውጤታማ የሚሆንበትን መንገድ ማፈላለግ ነው።

  ሁለተኛው የትርጉም ደንብ ግልፅ በሆኑ ጊዜ የዳኞችን ሃላፊነት የሚመለከት ነው። በፍትሃብሄር ህጉ አንቀፅ(1733)መሰረት ውሎች ግልፅ በሆኑ ጊዜ ግልፅ ሆኖ ከሚሰማው በመራቅ የተዋዋዮቹ ፍቃድ ምን እንደነበረ ዳኞች ሊተረጉሙ አይገባም እንደሚታወቀው ውል የሚይዠው የተዋዋዮችን ሃሳብ ነው። ግልፅ የሆነ ውል የተዋዋይ ወገኖችን ሃሳብ በቀጥታ የሚያስተላልፍ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል።

  ሶስተኛው የትርጉም ደንብ የተዋዋዮችን ሃሳብ አንድነት የሚመለከት ነው። በህጉ አንቀፅ(1734)መሰረት የውሉ ቃል የሚያሻማ በሆነ ጊዜ የተዋዋዮቹ ሃሳብ ምን እንደነበር ለማወቅ ጥረት መደረግ አለበት። ይህ ደግሞ ተዋዋዮቹ ውላቸውን ከመዋዋላቸው አስቀድሞ ወይም ከተዋዋሉ ቦሀላ የነበሩበትን ሁኔታ በማመዛዘን ተግባዊ የሚደረግ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ውሎች ጠቅላላ የሆነ አነጋገርን ይዘው የሚቀረፁበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ውሉ የሚፀናው ተዋዋዮቹ ሊዋዋሉበት የፈለጉ መስሎ የሚታየው ነገር ነው። አንቀፅ(1735)እነዚህ ደንቦች በዳኛው ላይ ከፍተኛ ሃላፊነትን የሚጥሉ ናቸው። በእርግጥም ተዋዋይ ወገኖች ከውሉ በፊት ወይም በኃላ የነበራቸው ሁኔታ ማጠየንና ከሚታወቁ ልማዳዊ ሁኔታ ጋር አገናዝቦ ውልን መተርጎም ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቅ ነው። እዚህ ላይ ፍትህ መስጠቱ ብቻ ሳይሆን ፍትህን ለማረጋገጥ የተሄደባቸውን ስርዐቶች ግልፅ ማድረግ ይገባል።

 ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች የትርጉም ደንቦች በፍትሃብሄር የተካተቱ በመሆኑ ውሉን መተርጎን አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ ከውሉ ባህሪ ጋር የሚቀራረበውን ትርጉም ከማይቀራረበው በመምረጥ ውሉን ዋጋ ከሚሳጣው ትርጉም ይልቅ ውጤታማ ሊያደርገው የሚገባውን የትርጉም ስልት መምረጥ እንዲሁም የውሉን ባለመብት ከሚጠቁመው ባለዕዳውን የሚደግፍ ትርጉም ተገቢ ስለመሆኑ የሚደነግጉትን ድንጋጌዋች በጥንቀቄ መመርመር ይገባናል።    

 ጉዳዩን የበለጠ ግልፅ ለማድረግ በሰ/መ/ቁ. 2543 የተሰጠዉን ዉሳኔ ማየት ይገባል፡፡

መጋቢት 25 ቀን  2000 ዓ.ም. 1996 ዓ.ም.  የፌ/ከ/ፍ/ቤት በመዝገብ ቁጥር 33291 መጋቢት 18 ቀን 1998 ዓ.ም. የሰጠው ፍርድ መሠረታዊ የህግ ስህተት ስላለበት በሰበር ይታረምልኝ በማለት አመልካች ሰኔ 13 ቀን 1998 ዓ.ም. በተፃፈ አቤቱታ ስለጠየቀ ነው፡፡ የክርክሩ መነሻ አመልካች 26 ኮንቴነሮችን በማስጫን ከተጠሪው ጋር ውል የነበረው መሆኑን ገልፆ፣ በመያዣነት ካስያዝኩት ገንዘብ ውስጥ ብር 104,190 /አንድ መቶ አራት ሺ አንድ መቶ ዘጠና/ አላግባብ ቀንሶ ስላስቀረና ከነሐሴ 3 ቀን 1990 ዓ.ም. ጀምሮ ከሚታሰብ ወለድ ጋር እንዲከፈል ይወስንልኝ በማለት አመልካች ያቀረበው ክስ ሲሆን፣ ተጠሪም በበኩሉ ክስ የቀረበበት ገንዘብ ከሳሽ ኮንቴነሮቹን በወቅቱ ባለመመለሳቸው እና ከሰላሣ ቀን በላይ በማቆየቱ መክፈል ያለበት መቀጫ ስለሆነ ሊመለስለት አይገባም በማለት ተከራክሯል፡፡

 

የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት የውሉ የቅጣት ድንጋጌ በክፍት ቢታለፍም በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1791 ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት ለደረሰው ኪሣራ ከሣሽ ካሣ መክፈል ስላለበት ቅጣቱም በቀን ብር 75 /ሰባ አምስት ብር/ መሆኑን ተከሣሹ ከሌሎች ደንበኞቹ ጋር ያደረገውን ውል በማስረጃነት ስላቀረበ ከሳሽ ቀሪ የማስያዥያ ገንዘብ ይመለስልኝ በማለት የቀረበውን ጥያቄ አልተቀበልነውም በማለት ወስኗል፡፡ አመልካች በዚህ ውሣኔ ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለፌ/ከ/ፍ/ቤት ያቀረበ ሲሆን የከፍተኛው ፍርድ ቤት የሥር ፍርድ ቤት የሰጠው ውሣኔ የሚነቀፍበት የፍሬ ጉዳይ እና የሕግ ምክንያት የለም በማለት ሠርዞታል፡፡ አመልካች በውል ሰነዱ መቀጫ ለመክፈል ያልተስማማንና የመቀጫ ድንጋጌው በክፍት /ዳሽ/ የታለፈ መሆኑ እየታወቀ ፍርድ ቤቱ ከሣሽ በክስ ማመልከቻው ያልጠየቀውን ኮንቴነሮቹ በወቅቱ ባለመመለሳቸው በተከሣሽ ላይ ካሣ የመክፈል ግዴታ አለባቸው በማለት ጭብጡን በመቀየር የወሰነ ስለሆነ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ፈጽሟል በማለት አመልክተዋል፡፡

 

ተጠሪው በበኩሉ ውሉ የቅጣት ድንጋጌ ያለው መሆኑን ጠቅሶ የቅጣት መጠኑ ባለመገለፁ ብቻ አመልካች አልተስማማም ማለት ስለማይቻል ይኸም በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1713 መሠረት ሊፈፀም ስለሚገባው የሥር ፍርድ ቤት የሰጠው ውሣኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት መልስ ሰጥቷል፡፡ አመልካች ባቀረበው የመልስ መልስ በሰበር አቤቱታው ላይ ያቀረባቸውን ነጥቦች በማጠናከር ተከራክሯል፡፡ የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት የሰጠው ውሣኔና ይግባኙ የቀረበለት ፍርድ ቤት የሰጠው ትእዛዝ እንዲሁም ግራ ቀኙ በሰበር ያቀረቡት ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም መዝገቡን መርምረናል፡፡ መዝገቡን እንደመረመርነው ተጠሪው አመልካች የጠየቀውን ገንዘብ በመያዣነት ተሰጥቶት ከነበረው ገንዘብ ውስጥ በመቀነስ ያስቀረ መሆኑ አልተካደም፡፡

 

ተጠሪው የሚከራከረው የቀነስኩት በውሉ መሠረት ከ30 ቀን በላይ ኮንቴነሮቹ ባለመመለሳቸው አመልካች መክፈል የሚገባውን የቅጣት ገንዘብ ነው በማለት ነው፡፡ በመሆኑም በአመልካችና በተጠሪ መካከል የተደረገው ውል፣ ኮንቴነሮቹ በመዘግየታቸው አመልካች ቅጣት ለመክፈል የተስማሙበት መሆኑን ያረጋግጣል ወይስ አያረጋግጥም? የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1791 ንዑስ አንቀጸ 1 መሠረት አመልካች ካሣ የመክፈል ኃላፊነት አለበት በማለት የሰጠው ውሣኔ ሕጋዊ መሠረት አለው ወይስ የለውም የሚሉትን ነጥቦች ማየት አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ የመጀመሪያውን ነጥብ በተመለከተ የውሉ አንቀጽ 4 ኮንቴነሩ ወደብ ከደረስ ከሰላሣ ቀን በኋላ፣ ኮንቴነሩ በቀን ብር ለመክፈል አመልካች ግዴታ መግባቱን ያሣያል፡፡ እንግዲህ በቀን ብር ዳሽ የሚለው የውሉ አራተኛው አንቀጽ እንዴት ነው መተርጎም ያለበት የሚለው የመጀመሪያው ነጥብ ነው፡፡ ተጠሪው፣ ይህ በቀን የሚከፈለውን የብር መጠን የማይገልጽ የውሉ አንቀጽ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1713 መሞላት አለበት በማለት የሚከራከር ቢሆንም ይኼ ድንጋጌ የዚህ አይነት አከራካሪና አጠራጣሪ ጉዳይ ለመፍታት አያገለግልም፡፡ እንደዚህ አይነት አጠራጣሪ ሁኔታ ሲያጋጥም የውሉ ድንጋጌ መተርጎም ያለበት በውሉ አስገዳጅ የሆነውን ወገን በሚጠቀምበት ሁኔታ ሣይሆን ለውሉ ተገዳጅ የሆነውን ወገን ምቹ በሚሆንበት አኳኋን መሆን እንደሚገባው አንቀጽ 1738 ንዑስ አንቀጽ 1 ይደነግጋል፡፡

 

ከዚህ አንፃር ስናየው አመልካች በየቀኑ የሚከፍለው የመቀጫ ገንዘብ መጠን የሚደነግገው የውሉ አንቀጽ አራት መተርጎም ያለበት ተጠሪውን በሚጠቅም መንገድ ሣይሆን በዚህ ድንጋጌ ተገዳጅ የሆነውን አመልካቹን በሚጠቅም መንገድ መሆን ይገባዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የውሉ አንቀጽ 4 ላይ የሚታየው ክፍተት አመልካች ለተጠሪው የቅጣት ገንዘብ  ያልተስማማ መሆኑን የሚያሣይ እንደሆነ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1738 ንዑስ አንቀጽ 1 ድንጋጌ መሠረት ለመረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህ አንፃር የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት በአመልካችና በተጠሪው መካከል የቅጣት ክፍያን አስመልክቶ ውል አለ ወይስ የለም የሚለውን ጭብጥ ከውል ድንጋጌዎች አተረጓጎም አንፃር አይቶ ሣይወስን ማለፉ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ሁለተኛውን ነጥብ በተመለተ፣ ተጠሪው ለቀረበበት ክስ፣የተከራከረው፣ ቀንሼ ያስቀረሁት ገንዘብ አመልካች በውላችን መሠረት ኮንቴነሮቹ ከሰላሣ ቀን በላይ ለዘገየበት በቀን ብር 75 /ሰባ አምስት ብር/ተሰልቶ መከፈል ያለበት የመቀጫ ገንዘብ ነው በማለት ነው፡፡

 

ተጠሪው የአመልካቹ ማለትም የሥር ከሣሽ ማመልከቻ ሲደርሰው በሥር ተከሣሽየሆነው ተጠሪው አመልካች በሰላሣ ቀን ውስጥ ኮንቴነሮቹን ባለማንሣቱ ደረሰብኝ የሚለው ኪሣራ በዝርዝር በመግለጽ አመልካች የውል ግዴታውን ባለመፈፀሙ ለደረሰበት ኪሣራ ካሣ ሊክሰኝ ይገባል የሚል፣ በተከሳሽ ከሳሽነት በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 234 ንዑስ አንቀጽ 1/ረ/ እና በፍትሐብሔር ሥነ ሥግዓት ሕግ ቁጥር 234 መሠረት አልጠየቀም፡፡ ተጠሪው አግባብነት ያላቸውን የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጎች መሠረት በማድረግና በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 215 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት አስፈላጊውን ዳኝነት ከፍሎ፣ ጥያቄውን ሣያቀርብ የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት አመልካች ኮንቴነሮቹን በወቅቱ ባለማንሣቱ በተጠሪው /ተከሣሽ/ ላይ ላደረሰው ጉዳት በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1791 ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት ካሣ የመክፈል ኃላፊነት አለበት በማለት በራሱ አነሳሽነት የሰጠው ውሣኔ፣ ከላይ የተገለጹትን መሠረታዊ የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ድንጋጌዎችና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተከራካሪዎች በግልጽ ባላቀረቡት እና በግልጽ ባላመለከቱት ጉዳይ ላይ ውሣኔ መስጠት አይቻልም የሚለውን የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 182 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረታዊ ድንጋጌ የሚጥስ በመሆኑም የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት የሰጠው ውሣኔና የፌ/ከ/ፍ/ቤት የሰጠው ውሣኔ የሕግ ወይም የፍሬ ጉዳይ ስህተት የለበትም በማለት የሰጠው ትእዛዝ መሠረታዊ የሕግ ስህተት አለበት በማለት ፍርድ ሰጥቷል፡፡

 

No comments:

Post a Comment

Cancellation of Contracts

   Cancellation of Contracts Cancellation is another remedy for non-performance. Cancellation brings an already existing contract to an end....