Sunday, March 7, 2021

ውል የሚፈርስባቸው ሁኔታዎች

(ምንጭ፡ የተሻሻለው የውል ህግ ሞጁል (ለሥራ ላይ ሠልጣኞች የተዘጋጀ)

ህግ የሚጠይቀውን ሥርዓት ተከትሎ የተሰራ ውል በህግ ፊት ሊፈጸም የሚችል ነው፡፡ የተዋዋዮችን ጥቅም የሚያስጠብቅ፣ ዕርካታን የሚያስገኝላቸው በመሆኑ እንደስምምነታቸው እንዲፈጸም የህጉ ፍላጎት ነው፡፡ ይሁንና ህጉ እንዲኖር የሚፈልገውን ወይም የሚጠይቀውን ሁኔታ የሚያሟላ ሳይሆን የገበያ ውድቀትን (market failure) ሊያመጣ የሚችል በመሆኑ ፍርስ ይሆናል ወይም እንዲፈርስ ይደረጋል፡፡ ይህ አይነቱን ችግር ያስከትላሉ የሚባሉት የሚከተሉት ሁኔታዎች ናቸው፡፡

የፈቃድ ጉድለት

ውል ተነፃፃሪ ግዴታዎቻቸውን ተረድተው ጥቅሞቻቸውን ለማስከበር በሚችሉ ሰዎች መካከል የተፈጸመ መሆን አለበት፡፡ አንዳንድ ሰዎች በዕድሜ ማነስ፣ በመጃጀት ወይም በአዕምሮ ጤንነት ጉድለት ምክንያት ጥቅሞቻቸውን ተገቢ በሆነ መንገድ (rationally) ለማስጠበቅ ይችላሉ ተብሎ አይታሰብም፡፡ ይህ ህጉ የሚፈልገውን የጋራ ጥቅም የሚያስገኝ አይሆንም፡፡ እነኚህ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው ለአደጋ የተጋለጡ ክፍሎች ስለሆኑ ህጉ ከለላ ይሰጣቸዋል፡፡ ስለሆነም የፈፀሙት ውል እንዲፈርስ ይደረጋል፡፡ ይህን ማድረግ የሚችለውም በውሉ ተጎድቻለሁ የሚለው ወገን ብቻ ነው፡፡ ችሎታ ማጣቱን መከላከያ ሊያደርገው የፈለገ እንደሁ ውሉ በተደረገ ጊዜ ችሎታ እንደልነበረው ማስረዳት ይጠበቅበታል፡፡ ምክንያቱም ህጉ ማንኛውም ሰው ችሎታ አለው የሚል ግምት የሚወስድ በመሆኑ፡፡ ፍርስ ከመሆን ይልቅ ፈራሽ እንዲሆን የተደረገው  ጠቃሚ የሆኑ የኢኮኖሚ ልውውጦች በየሰበቡ እንዳይታጎሉ ለማድረግ ነው፡፡  

በተመሳሳይ ሁኔታም ህጉ መሰረታዊ ነው ብሎ የሚጠይቀው የነፃ ፈቃድ መኖር ለአንድ ውል ህልውና ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ በነፃ ፈቃድ ላይ ያልተመሰረተ ስምምነት የጋራ የሆነ የኢኮኖሚ ጥቅምን (economic welfare) ዋጋ የሚቀንስ ነው፡፡ ስለሆነም ህጉ በነፃ ፈቃድ ላይ ያልተመሰረተ ስምምነትን አያበረታታም፡፡ ቀደም ሲል በነበረው ክፍል እንደተገለጸውም አስተማማኝነትን የሚያጎድል፣ በግለሰብም ሆነ በህብረተሰብ ደረጃ የሚኖረውን ትርምስ ለመቆጣጠር ከፍ ያለ ወጪን የሚጠይቅ በመሆኑ ተፈላጊውን ስልጠት አያስገኝም፡፡ ስለሆነም በፈቃዱ ጉድለት የተደረገውን ስምምነት እንዲፈርስለት ተጎጂው እንዲጠይቅ ህጉ እድል ይሰጠዋል፡፡

ለአንድ ተወዳዳሪ ገበያ (competitive market) መኖር አስፈላጊ ነው የሚባለው በቂ መረጃ ነው፡፡ በቂ መረጃ በሌለበት ሁኔታ የገበያው ተሳታፊዎች በሂደቱ ደስታን በሚያስገኝላቸው መንገድ የጋራ ጥቅማቸውን ያስከብራሉ ተብሎ አይታሰብም፡፡ ስለሆነም ህጉ ቀና የሆነ የገበያ ውድድርን ለመጠበቅ ሲል በቂ መረጃ እንዳይኖር ዕንቅፋት የሚፈጥረውን አጋጣሚ አያበረታታም ስለዚህም በስህተት፣ በተንኮል እና በመጎዳት (unconscionability) የሚደረጉ ስምምነቶች ሲኖሩ ተዋዋዩ ውሉን እንዲያፈርስ ዕድል ይሰጣል፡፡

ከዚህ አኳያ በፌደራል ጠ/ፍ/ቤት በሰ/መዝ/ቁ 20232 ሐምሌ 24 ቀን 1999 ዓ.ም የተሰጠውን ውሳኔ መመልከቱ ከፍቃድ ጉድለት ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ ጉዳዮችን በጥንቃቄ እንድንመረምር ይረዳል የሚል እምነት አለ።

  

 መዝገቡ ለሰበር ችሎት ሊቀርብ የቻለው  አመልካች ነሐሴ 17 ቀን 1997 ዓ.ም ጽፈው ባቀረቡት አቤቱታ መሠረት ሲሆን የጉዳዩ መነሻ አመልካች ጥቅምት 14 ቀን 1989 ዓ.ም ከተጠሪ ጋር ያደረጉት ውልና ለውሉ ማረጋጫና ማስፈፀሚያነት በዚሁ ቀን በቁጥር ኢዲ 657900 የሆነቼክ ብር 90,000 (ዘጠና ሺህ) የካቲት 1 ቀን 1989 ዓ.ም የሚከፈል ለተጠሪ ከሰጡ በኋላ ገንዘቡ እንዳይከፈል አግደውብኛል በማለት ተጠሪ በሥር ፍ/ቤት ክስ አቅርቦ የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት ግራቀኙን ካከራከረ በኋላ አመልካች ያቀረቡትን መቃወሚያ ውድቅ በማድረግ በቀረበው ክስ መሠረት በቼኩ የተመለከተውንገንዘብ የሥር ተከሣሽ (አመልካች) እንዲከፍሉ ወስኗል። የፌ/ከ/ፍ/ቤትም ይህንኑ ውሣኔ አፀናው።

 

     ለሰበር የቀረበው አቤቱታ አመልካች ቼኩን የሰጠው ተገዶ ያለፍቃዱና ያለፍላጐት መሆኑን በማስረጃ ተረጋግጦ እያለ የውል ህጐች መሠረታዊ መርሆዎች በግልጽ ተጓድለው እያሉ የሥር ፍ/ቤት የቀረበውን ሠነድ ሕጋዊ እንዳልሆነ እና ውሉ ጉድለት እንደሌለበት አድርጐ የሰጠው ውሣኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለው በመሆኑ እንዲሻርለት ጠይቋል። የሰበር ችሎትም መዝገቡን ከመረመረ በኋላ ይህንኑ ቅሬታ ለማጣራት ተጠሪ እንዲቀርብ ያዘዘ ሲሆን ተጠሪው ሊቀርብ ባለመቻሉ ጉዳዩ በሌለበት እንዲታይ ሰኔ 7 ቀን 1999 ዓ.ም በዋለው ችሎት አዟል።  በዚሁ ሁኔታ መዝገቡ ተመርምሯል። ከቀረበው አቤቱታና ከሥር ፍ/ቤት ውሣኔ አንፃር አመልካች ቼኩን የፈረምኩት ተገድጄ ነው በማለት ያቀረበው የሕግ ክርክር ውሉን ፈራሽ ያደርገዋል ወይስ አያደርገውም የሚለውን እንደሚከተለው ከውል ሕጐች መሠረታዊ መርህ ጋር በማገናዘብ ተመልክቷል።

 

      በፍሬ ነገር ክርክር ደረጃ በሥር ፍ/ቤት ውሣኔ እንደተብራራው አመልካች ለተጠሪ የብር 90,000 (ዘጠና ሺህ) ተከፋይ ቼክ ጥቅምት 14 ቀን1989 ዓ.ም መስጠቱን አልካደም። ሆኖም በቼኩ ክፍያ አለመፈፀም ያቀረበው መቃወሚያ ቼኩና ውሉ የተፃፈው ተጠሪ በወረዳ 5 ፖሊስ ጣቢያ አሳስሮት በእሥር ላይ ሆኖ ተገዶ የፈረመው ስለሆነ እና በዚሁ ወንጀል የፖሊስጣቢያው አዛዥና መርማሪ ፖሊስ በወንጀል ተከሰው በአቃቤ ህግ ክስየተመሠረተባቸው መሆኑን በመግለጽ ለዚህም የሰውና የሰነድ መከላከያማስረጃ በማቅረብ በቼኩ የተመለከተውን ገንዘብ ለመክፈል እንደማይገደድ ተከራክሯል። የሥር ፍ/ቤትም ይህንኑ ጉዳይ ለማጣራት አመልካች ያቀረባቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ከመረመረ በኋላ ቼኩን ለማስፈረም የኃይል ሥራ ተፈጽሟል ለማለት አይቻልም በማለት መቃወሚያውን ውድቅ ኣድርጓል።

 

    በሥር ፍ/ቤት ውሣኔ ውስጥ እንደተመለከተው የማስገደድ ተግባር በመልካች ላይ ስለመፈፀሙ የቀረበው የሰውና የሰነድ ማስረጃ እንዲሁም በወቅቱ የፖሊስ ጣቢያው አዛዥ በነበረው ግለሰብ ላይ የቀረበው የወንጀል ክስ በፌ/ከ/ፍ/ቤት በወ/መ/ቁ. 07009 ጥቅምት 11 ቀን 1998 ዓ.ም በልዩ ወ/መ/ሕግ አዋጅ ቁጥር 214/74 አንቀጽ 23-1ሀ መሠረት የተሰጠውየጥፋተኛነት ውሣኔ ሲታይ በወቅቱ አመልካች ውሉን የተዋዋለው በአስገዳጅ ሁኔታ ሥር ሆኖ እንደነበር የሚያረጋግጡ ናቸው።

 

    ይህ ሁኔታ ከሕጉ አንፃር ምን ውጤት ሊኖረው ይችላል የሚለውን ለማጤን ከውል መሠረታዊ መርህ ጋር መጤን አለበት። ቼክ የሚተላለፍ የገንዘብ ሰነድ መሆኑ በንግድ ሕግ ቁጥር 715 የተመለከተ ነው። በእነዚህ የሚተላለፉ የገንዘብ ሰነዶች የተዋዋይ ወገኖች መብትና ግዴታዎች የሚፈጠሩባቸውና የሚረጋገጡባቸው ናቸው። የሰነዱ አውጪ ግዴታ የሚገባበት ሲሆን የሰነዱ አምጪ /ያዢ/ የመብት ወይም ጥቅም ማረጋገጫ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ይህንን ሁኔታ ለመፍጠር እንደማንኛውም ውሎች የውል ህግ መሠረታዊ ድንጋጌዎች መሟላት እንዳለባቸው የሚያከራክር አይደለም። ምክንያቱም እነዚህ የሚተላለፉ የገንዘብ ሰነዶች መሠረት በባህሪያቸውና በዓላማቸው ልዩ ቢሆንም ተዋዋይ ወገኖች በዚህ ሰነድ መብትና ግዴታ ለመፍጠር የውል ሕግ አጠቃላይ መርሆዎችን አሟልተውና አክብረው መገኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከእነዚህ መሠረታዊ መርሆዎች ውስጥ አንደኛው ውሉን ለመፈፀም (ለመዋዋል) የተዋዋይ ወገኖች ፈቃደኛነትና ነፃነት መኖር አስፈላጊነት ነው፡፡ ውል በተዋዋይ ወገኖች ሙሉ ፈቃደኛነት ላይ ካልተመሠረተ በሕግ ፊት የፀና ሊሆን አይችልም በመሆኑም የውል መፈረስ ምክንያት ከሚሆኑት መሠረታዊ ነገሮች አንዱ በውል አመሠራረት ሂደት ውስጥ በአንደኛው ወገን የሚፈፀም የኃይል ወይም የማስገደድ ተግባር ነው፡፡ ይህ መሠረታዊ መርህ በፍ/ብ/ሕግ ቁጥር 1679 ስር በግልጽ ተደንግጓል፡፡ ይህንን መሠረታዊ መርህ በዝርዝር የሚያመለክተው የፍ/ብ/ህግ ቁጥር 1706 እና ተከታዩ የማስገደድ ተግባሩ በማን ተፈፀመ? እንዴትስ ተፈፀመ? በማን ላይ ተፈፀመ የሚሉትን ሁኔታዎች በዝርዝር አመልክቷል፡፡

 

     አሁን በቀረበው ጉዳይ ላይ ከላይ በዝርዝር እንደተመለከተው ኣመልካች ቼኩን የፈረመው በፖሊስ ጣቢያ ታስሮ በፖሊስ ጣቢያው አዛዥ አስገዳጅነት እንደሆነ በቀረቡት ማስረጃዎች በሥር ፍ/ቤት ተረጋግጧል፡፡ በዚህ አይነት አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የተደረገው ውል ፈቃደኛነትና የመዋዋል ነፃነት ጉድለት ያለበት መሆኑን መገንዘብ የሚያዳግት አይደለም፡፡ ይህ ሁኔታ በተፈጠረ ጊዜ ደግሞ ውሉን ስለመፈፀም መቃወሚያ አድርጐ ማቅረብ ስለመቻሉ በንግድ ሕግ ቁጥር 841 ተመልክቷል፡፡

 

     በዚህ የንግድ ሕግ ቁጥር 841 ድንጋጌ መሠረት የቼኩ አውጪ በአምጪው ላይ መቃወሚያ ሊያደርግ የሚችለው ቼኩን ያገኘው ቅን ልቦና በጐደለው ሁኔታ ወይም ቼኩን ሲያገኝ ከባድ ጥፋት ያደረገ መሆኑ ሲረጋገጥ እንደሆነ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት አሁን የቀረበው” የቼክ ክፍያ ጥያቄ በተመለከተ ተጠሪው ቼኩን ከአመልካች ያገኘው ቅን ልቦና በጐደለው ሁኔታ ከመሆንም አልፎ በማስገደድ ተግባር በመሆኑ ከባድ ጥፋት መፈፀሙ ተረጋግጧል፡፡

 

    ስለዚህ አንድ የኃይል ሥራ ወይም የማስገደድ ተግባር አንድ ተዋዋይ ወገን ሳይወድና ሳይፈቅድ ከፍላጐቱ ውጪ የውል ግዴታ እንዲገባ ለማስገደድ በቃላት ወይም በድርጊት የሚፈፀም ሕገ ወጥ ማስፈራት ወይም ዛቻ ወይም በአካል ላይ የሚፈፀም አድራጐት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በአመልካች ላይ የተፈፀመው የማስገደድ ተግባር እሥር እና ዛቻ መሆኑ በሥር ፍርድ ቤት ተረጋግጦ እያለ የሥር ፍ/ቤት በምን ተገደደ በዱላ ወይስ በሌላ በማለት ጭብጥ በመያዝ የመገደድ ተግባር አልተፈፀመበትም በማለት የወሰደው አቋምና የሰጠው ውሣኔ መሠረታዊ የሕግ አተረጓጐም ስህተት ያለበት ሆኖ አግኝተነዋል ብሏል፡፡ መሠረታዊ የሆነውን የፈቃደኛነትና የመዋዋል ነፃነትን የሚጋፋ ተግባር ተፈጽሞ እያለ ጉድለት የለበትም ማለት ሕግ ለተዋዋይ ወገኖች የመዋዋል ነፃነት ያደረገውን ጥበቃ በእጅጉ የሚያላላ ውሣኔ ሆኖ በመገኘቱ የሥር ተከሣሽ የአሁን አመልካች ያለፈቃዱ እና ፍላጐቱ ተገዶ በፈረመው ቼክ ክፍያ ሊገደድ አይገባም ብለናል፡: ስለዚህ የአመልካች መቃወሚያ በንግድ ሕጉ ቁጥር 841 እና በፍ/ብ/ሕግ ቁጥር 1679 መሠረት ተቀባይነት የለዉም በማለት የስር ፍርድ ቤቶች የሰጡትን ዉሳኔ ሽሯል፡፡

ስለዚህ ግልፅ መስለው የሚታዩ አንዳንድ ጉዳዮች በጥንቃቄ ካልታዩ ውጤታቸውም ፍትሃዊ ሊሆን አይችልም።     

  ከህግ ውጪ እና ለሞራል ተቃራኒ መሆን

ማንኛውም ውል የህብረተሰቡን ጠቅላላ ጥቅም ለመጠበቅ በተዘጋጀው የህግ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲከናወን ይፈለጋል፡፡ ማኅበራዊ ህጉን (pubic law) ፣ ፖሊሲዎችን በሚቃረን መንገድ የተፈጸመ እንደሆነ ዕውቅና አያገኝም፡፡ ይህን መጣስ ተፈላጊውን ማህበራዊ ፍትህ አያስገኝም፡፡ ስለሆነም አይበረታታም፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፡፡ ህብረተሰቡን ከሚያስተሳስሩት ማህበራዊ ዕሴቶች ውስጥ አንዱ የኔ ናቸው፣ ሊጠበቁልኝ ይገባል የሚላቸውን የሞራል ዋጋዎች (moral values) መጠበቅ አንዱ የህጉ ዓለማም ነው፡፡ ስለሆነም እነኚህን ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ ያላስገባ ስምምነት ዕውቅና አይሰጠውም፡፡ ፍርስ እንደሆንም ይታሰባል፡፡

  ህጉ የሚጠይቀውን የአፃፃር ሥርዓት ተከትሎ የተሰራ አለመሆን

ውሎች በተዋዋዮች ፈቃድ ላይ የተመሰረቱ መሆን አለባቸው፡፡ እንዴት እና በምን ዓይነት ሁኔታ መዋዋል እንደሚፈልጉ የሚወስነት እነሱው ናቸው፡፡ ህግ ጣልቃ አይገባም፡፡ ይሁንና የህብረተሰቡን ጠቅላላ ጥቅም ከማስጠበቅ አንጻር የተወሰኑ ገደቦች ይጣሉባቸዋል፡፡ አንዱ ህጉ ወሳኝና አስፈላጊ ናቸው በሚላቸው የውል ዓይነቶች ላይ ተዋዋዮች ሊከተሉ የሚገባውን የአፃፃፍ ሥርዓት የሚመለከት ነው፡፡ የተለየ የአፃፃፍ ሥርዓት እነዲከተሉ በህግ የታዘዘ በሆነ ጊዜ የህጉ ቃል መከበር አለበት [1678 (3) (ሐ)] ፡፡ ይህ ማለት ህጉ በመርህ ደረጃ በፈቃድ ላይ የተመሰረተ ከመሆን አልፎ ፎርምን በመርህ ደረጃ አይጠይቅም ማለት ነው፡፡ 

ስምምነቶች አንድ ዓይነት የአፃፃፍ ሥርዓትን እንዲከተሉ የሚፈለግበት ምክንያት

1.   ህጉ ዋና ናቸው በሚላቸው ጉዳዮች ላይ የተዋዋዮቹን ጥቅም አስተማማኝ በሆነ መንገድ ለመጠበቅ ታስቦ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ውል በጽሁፍ እንዲሆን መታዘዙ የውሉን ይዘት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ያቀላል፡፡ በዚህ ረገድ ሊኖር የሚችለውን ውዝግብም ይቀንሳል፡፡ በዚህ የተነሳም የሰዎችን የውል ግንኙነት ውጤታማ በሆነ መንገድ መምራት ይቻላል ማለት ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊ በሆነ አስተሳሰብም ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጊዜ፣ ወጪ እና ድካምን በመቀነስ  ስልጠትን የሚፈጥር ነው፡፡

 

2.   ተዋዋዮች በችኮላ ቃል ከመግባታቸውና ይህም በነርሱ ላይ አስገዳጅ ከመሆኑ በፊት በጉዳዩ ላይ እንዲያስቡበት የአፍታ ጊዜ እንዲያገኙ (precautionary role) ማድረግ ነው፡፡

ደካማውን ተዋዋይ ወገን ለመጠበቅም ይረዳል፡፡ ሌለው ወገን ማስረጃው እንዲደርሰው በመጠየቅ የመደራደር አቅም የሌለውን ተዋዋይ ጥቅም ያስጠብቃል (protective function)፡፡ በአሠሪና ሠራተኛ ህግ ላይ አሠሪው ለሠራተኛው መቀጠሩን በጽሁፍ እንዲያሳውቀው እንደሚያዘው ማለት ነው፡፡  ታዲያ በነኚህ መሰረቶች ላይ የቆመውን ዓለማ ለማሳካት ውሉ ውጤት እንዲኖረው ከመደረጉ በፊት የተጠየቀውን ሥርዓት ማሟለቱን ማረጋገጥ ይጠይቃል፡፡ ከተዋዋዮች እንዲነሳ ሳይጠበቅ ፍርድ ቤቱ ሊያነሳው የሚችለው ጉዳይ ነው፡፡ የህጉን ዓላማ ለማስፈፀም ከፍርድ ቤቶች የተሸለ ዕድል ያለው የለም፡፡ ስለሆነም ፍርድ ቤቶች በዚህ ረገድ ንቁ መሆን ይገባቸዋል፡፡    

No comments:

Post a Comment

Cancellation of Contracts

   Cancellation of Contracts Cancellation is another remedy for non-performance. Cancellation brings an already existing contract to an end....