Sunday, March 7, 2021

የውል ህግ አወቃቀር

(ምንጭ፡ የተሻሻለው የውል ህግ ሞጁል (ለሥራ ላይ ሠልጣኞች የተዘጋጀ)

የኢኮኖሚ ስልጠትን መፍጠር

ቀደም ሲል እንደተገለጸው ውል ንብረቶቻቸውን የተመለከቱ ግዴታዎችን ለማቋቋም፣ ለመለወጥ ወይም ለማስቀረት ባላቸው ተወዳዳሪ ግንኙነት የተነሳ ሰዎች በመካከላቸው የሚመሰረቱት ስምምነት ነው ብለናል፡፡ የግንኙነታቸው መሰረት ንብረት ነው፡፡ ወጪን ያንራል፣ በገበያ ላይ ያለን መተማመን ያጎድላልና ሰዎች ንብረቶቻቸው ከአንዱ ወደ ሌላው ሲያሳልፉ የልውውጡ ፍሰት እንዲታጎል አይፈልጉም፡፡ ይህ የተዋዋዮች ብቻ ሳይሆን የጠቅላላው ሕዝብ ፍላጎትም ጭምር ነው፡፡ ይህ እንዲሆን ታዲያ የውል ህግ የገበያው ተሳታፊዎች ሊኖራቸው የሚገባው ጠባይ ምን መሆን፣ እንዴት መመራት እንዳለበት ደንብና ሥርዓት በማበጀት የልውውጡ ሂደት መተማመን ያለበት ጊዜና ወጪን የሚቆጥብ የሰዎችን ዕርከታ የሚያስገኝ እንዲሆን ተደርጎ ይዋቀራል፡፡ ስለሆነም የውል ህግ በሰዎች መካከል ያለውን ቀና የሆነ የኢኮኖሚ ግንኙነት የሚገዛ መሳሪያ ነው ቢባል ስህተት አይሆንም፡፡

ነገሩን ለማብራራት ያህል ስልጠት ከሰዎች ርካታ አንጻር ሊገለጽ ይችላል፡፡ አንድ መጽሀፍ የገዛ ሰው ለገዛው መጽሀፍ የከፈለው ዋጋ መጽሀፉ ለርሱ ከሚሰጠው ጠቀሜታ አንጻር ሲታይ ጥሩ ነው ማለት ይቻላል፡፡ አነስተኛ ዋጋ ሊሰጠው የሚችል ሌላ ሰው አለ ተብሎ አይታሰብም፣ ቢታሰብም ራሱን የቻለ የጊዜና የገንዘብ ወጪ ሳይጠይቅ የሚፈፀም አይሆንም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መጽሀፉን የሸጠው ሰው በበኩሉ ስለመጽሀፍ ሽያጭ የተቀበለው ዋጋ ዕርካታን ይሰጠዋል በተመሳሳይ ዋጋ መጽሀፍን የሚገዛው ሰው ባለመኖሩ ከሽያጩ ደስታን አትርፏል፡፡ እንዲህ ሲሆን ሸቀጦች (resources) ከፍ ያለ ተጠቃሚነት ወደሚያገኙት ሰዎች ተሸጋግሯል ማለት ይቻላል፡፡ ስልጠት ማለትም ሀብቶችን ለሰዎች ከፍተኛ ዕርካታን በሚያስገኝ በዚህ ዓይነት መንገድ መጠቀም ማለት ነው፡፡ ህጉ ይህንን እንዲያበረታታ ተደርጎ የተቀረጸ ነው፡፡ ሰው በቃሉ ይታሰራል የሚለውን መርህም አንዱ የዚህ ማስፈጸሚያ መሳሪያ አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡

በአንፃሩ አንድን ሸቀጥ በማታለል ወይ በኃይል ያገኘ ሰው ቢኖር በዚህ መንገድ የተደረገው ልውውጥ የኢኮኖሚ ስልጠትን የሚያስገኝ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም አንዱ ወገን መረጃን  በሞኖፖል መያዝ ብቻ ሳይሆን መረጃን በማሳሳት ወይም ደግሞ ከተዋዋዮቹ ውስጥ የአንዱ የመደራደር አቅም በማይገባ ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ ላይ መገኘቱ መተማመንን በማጉደል የገበያ ውድቀትን የሚያስከትል በመሆኑ ነው፡፡ በግለሰብም ሆነ በህብረተሰብ ደረጃ ሁኔታውን ለመቆጣጠር ከፍ ያለ ወጪን ይጠይቃል፡፡ እናም የኢኮኖሚ ስልጠትን አይፈጥሩም፡፡ ህጉ ይህን አያበረታታም፡፡ መገደድ እና ማታለልን የማይደግፉ ህጎች የተቀረጹትም እንዲህ ያሉ የኢኮኖሚ ስልጠት የማይፈጥሩ ጠባያትና ሁኔታዎችን በመቆጠጠር ተፈላጊውን ስልጠት ለማስገኘት ሲባል ነው፡፡ 

ስለሆነም ህጉ ብቸኛው ባይሆንም አንድ የኢኮኖሚ ስልጠትን የሚያስገኝ መሳሪያ ተደርጎ ሊወሰድ ይቻላል ማለት ነው፡፡

ኪሣራን ማሸጋገር

ሸቀጦች በጊዜ ሂደት የዋጋ ልዩነት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ይህ ፍርሀትን ይፈጥራል፡፡ በዚህ የተነሳ ሰዎች በመጪው ጊዜ በሚኖረው የዋጋ ልዩነት ተጎጂ እንዳይሆኑ ከወዲሁ ስምምነት በማድረግ የወደፊቱን ዋጋ ዛሬ ላይ ለማሰር ይገፋፋሉ፡፡ ሱራፌል በመጪው ሰኔ በብር 150 አንድ ኩንታል ስንዴ ሊያስረክበኝ ቃል ባይገባ ኖሮ ሰኔ ሲደርስ በብር 250 ለመግዛት እሱም ቢሆን ዋጋው ሲወርድ በወረደው በብር 50 ዋጋ ስንዴውን እንደቅደም ተከተላችን ለመግዛትና ለመሸጥ እንገደድ ነበር፡፡ ስምምነት ከተደረገበት ዋጋ አንፃር የወጣውን ወይም የወረደውን ዋጋ ልዩነት ስናይ የልዩነቱ መጠን በአንዳንችን ላይ ሊደርስ ይችል የነበረው በስምምነት አንዳችን በሌላችን ላይ ያስተላለፍነው ኪሳራ ነው፡፡ በመሰረቱ ማንኛውም ሰው በሚፈፅመው ውል ላይ ይህን አገላለጽ ቃል በቃል ላያገኘው ይችላል፡፡ ይሁንና የስምምነቱ ይዘት በጥልቀት ሲመረመር የሚያሳየው ይህንኑ ነው፡፡

ታዲያ የተደረገውን ስምምነት የሚያስፈጽም የውል ህግ ባይኖር መጪውን ጊዜ ባየነው መጠን የሚደርሰውን ኪሳራ ለማስተላለፍ ባልተቻለን ነበር፡፡ አሁን ግን ተዋዋዩ በስምምነታችን መሰረት ስንዴውን ሊያቀርብልኝ ይገደዳል፤ በርክክቡ ጊዜ ባለው ዋጋ መሸጡ የበለጠ ሊያተርፈው ቢችል እንኳ የውሉን ግዴታ ከመፈጸም ሊሸሽ አይችልም፡፡ መሸሽ ቢችልም በርክክቡ ጊዜ ስንዴ ለመግዛት የምገደድበትን የኪሳራ ገንዘብ እንዲተካ ይገደዳል፡፡ ህጉ ይህን ዓይነት ግንኙነት እንዲያበረታታ ሆኖ የተቀረጸ ነው፡፡

ይህ ብቻም አይደለም፡፡ ተዋዋዮች በስምምነታቸው ላይ ሳያሰፍሩት በቀሩ ጊዜ እንኳ ህጉ ለውሉ አለመፈፀም ምክንያት የሆነውን ችግር በተሻለ ሁኔታ ለመቆጣጠር ማን ይችል እንደነበር ከግምት ውስጥ በማስገባት ኪሳራን ያሸጋግራል (1802)፡፡    

ማህባራዊ ፍትህ እና ርትዕን ማስፈን    

እስከሁን ያነሳናቸው በአብዛኛው ከኢኮኖሚ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ይህ ማለት ግን ውል በኢኮኖሚክ አመክንዮ ብቻ የተተበተበ ነው ማለት አይደለም፡፡ በውል ስምምነት ውስጥ እንዲኖር የሚፈላገውን ነፃነት ከተጠያቂነት ጋር አጣጥሞ በማየትም ማህበራዊ ፍትህን የሚያሰፍን መሳሪያ ጭምር ተደርጎ ሊታይ ይችላል፡፡ ለምሳሌ የተዋዋዮች ስምምነት በነፃ ፈቃዳቸው ላይ የተመሰረተ መሆን ይገባዋል፡፡ አንዱ ወገን የሌላውን ፈቃድ ያገኘው በማስገደድ እንደሆነ እንዲህ ያለውን አጉል ጠባይ በመቆጣጠር አቅም የሌላቸውን ሰዎች ጥቅም ይጠብቃል፡፡ እናም ማኅበራዊ ፍትህን ያሰፍናል፡፡

ርትዓዊ ከመሆን አንጻርም አንዳንድ ግንኙነቶች የሚፈጥራቸውን ውጤቶች ከማኅበራዊው አኗኗር መለኪያ አንፃር እየታየ እንዲመዘን የሚፈቅድም ነው፡፡ ውጤቶቹ ፍትሀዊ መስለው በማይታዩ ጊዜ በተለያዩ ቦታዎች ዳኞች በርትዕ እንዲወሰኑ ህጉ መብት የሚሰጣቸውም በዚህ መነሻ ነው፡፡ ህጉ ስለ መጎዳት (unconscionability) እና ስለ ቅን ልቡና የሚያነሳውም ከዚሁ የርትዕ ጉዳይ ጋር የተያያዘ መሆኑን ማጤን ይገባል፡፡  

No comments:

Post a Comment

Cancellation of Contracts

   Cancellation of Contracts Cancellation is another remedy for non-performance. Cancellation brings an already existing contract to an end....